በግማሽ በጀት ዓመት ውስጥ ከ 556 ኪሎ ሜትር በላይ የግንባታና የጥገና ስራዎች ተከናውነዋል
አዲስ አበባ፣ ጥር 8 ቀን 2016 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በ2016 በጀት ዓመት ግማሽ ዓመት ውስጥ 464.9 ኪሎ ሜትር ልዩ ልዩ የግንባታና የጥገና ስራዎች ለመስራት አቅዶ 556 ኪ.ሜ በማከናወን ከዕቅድ በላይ ለማሳካት ችሏል፡፡
በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያው ግማሽ ዓመት ውስጥ ከተከናወኑት የግንባታ ስራዎች መካከል 16.39 ኪ.ሜ የአስፋልት፣ 12.71 ኪ.ሜ የጠጠር፣ 4.45 ኪ.ሜ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የውስጥ ለውስጥ የኮብል መንገዶች፣ 21.87 ኪ.ሜ የኮብል ንጣፍ፣ 27.6 ኪ.ሜ የእግረኛ መንገድ መልሶ ግንባታ፣ 5.8 ኪ.ሜ የዲሬኔጅ መስመሮችና የድጋፍ ግንብ ስራዎችን የሚያካትት ሲሆን በድምሩም 88.84 ኪ.ሜ ይሸፍናል፡፡
በተመሳሳይም በተለያዩ ምክንያቶች ለብልሽት የተዳረጉ 45.87 ኪ.ሜ የአስፋልት፣ 15.17 ኪ.ሜ የጠጠር እና 14.84 ኪ.ሜ የኮብል መንገዶች ጥገና ተከናውኗል።
በሌላም በኩል 301.2 ኪ.ሜ የሚሸፍን የድሬኔጅ መስመሮች ፅዳት፣ 2.94 ኪ.ሜ የድሬኔጅ መስመር ዕድሳትና ጥገና፣ 2.41 ኪ.ሜ የእግረኛ መንገድ መከለያ አጥር ስራ እና 9.78 ኪ.ሜ የእግረኛ መንገድ ጥገናና የከርቭ ስቶን ስራዎች ተሰርተዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም 74.97 ኪ.ሜ የመንገድ ቀለም ስራዎችን በማከናወን በጠቅላላው 467.18 ኪ.ሜ የሚሆን ልዩ ልዩ የመንገድ ጥገና ስራዎችን በበጀት ዓመቱ ግማሽ ዓመት ውስጥ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡
የከተማዋን የምሽት ክፍለ ጊዜ የትራፊክ እንቅስቃሴ ምቹ ለማድረግ ከ7 ሺህ በላይ የመንገድ መብራት ምሰሶዎችና የመስመር ጥገና ማካሄድ በበጀት ዓመቱ የመጀመሪያ መንፈቅ ዓመቱ ከተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት መካከል የሚካተቱ ናቸው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity