+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ከመንገድ መሰረተ-ልማት ባለድርሻ አካላትና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጥር 3 ቀን 2016 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ዋርካ የቴሌቪዥን ፕሮግራም ጋር በመተባበር ከመንገድ መሰረተ-ልማት ባለድርሻ አካላትና ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

በምክክር መድረኩ ላይ ከታሳታፊዎች የተነሱ ጥያቄያዎች ላይ ምላሽ የሰጡት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ ባለፉት 5 የለውጥ ዓመታት በተካሄደው መጠነ ሰፊ የመንገድ ግንባታ ሥራ የከተማዋ የመንገድ ኔትዎርክ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፤ በከተማዋ እየተከናወነ የሚገኘውን የመሰረተ-ልማት ተደራሽነት ማስፋፋት ተከትሎ የህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት እየጨመረ መምጣቱን ገልፀዋል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሞተር አልባ ትራንስፖርት ልዩ ትኩረት በመስጠት በተያዘው በጀት ዓመት 18 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን የፔዳል ሳይክል መተላለፊያ መንገድ ግንባታ በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ለማብቃት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀው፤ ባለፉት አምስት ዓመታትም ከ170 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት የሚሸፍኑ የእግረኛ መንገዶችን መልሶ በመገንባት ለአገልግሎት ማብቃቱን ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም ባለስልጣን መስርያ ቤቱ በከተማዋ የሚሰተዋለውን የመንገድ ዳር የውሃ መፋሰሻ መስመር ችግር በዘላቂነት ለመፍታት የድሬኔጅ መስመር ማስተር ፕላን ዲዛይን ስራ እያጠናቀቀ እንደሚገኝ ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘው ገልፀዋል ፡፡

ይሁን እንጂ በመንገድ ሀብት አጠቃቀም ችግር በከተማዋ የሚገነቡ መንገዶች ረጅም ጊዜ አገልግሎት ሳይሰጡ እየተበላሹ እንደሚገኙ ገልፀው፤ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ አገለግሎት እ ንዲሰጡ በማድረግ በኩል የባለድርሻ አካላት እና የህብረተሰቡ ሚና የጎላ በመሆኑ ሁሉም አካላት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ኢንጂነር ሞገስ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የከተማዋን የመንገድ ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ ለማሳደግ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው፤ ሁሉም መሰረተ ልማት አቅራቢ ተቋማት ቅንጅታዊ አሰራራቸውን ይበልጥ በማጠናከር የሀብት ብክነት ለመከላከል በትኩረት መስራት እንደሚገባቸው ጠቁመዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.