+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በከተማዋ በግንባታ ላይ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ጥር 1 ቀን 2016 ዓ.ም፡-“የባለድርሻ አካላትና የህብረተሰብ የላቀ ተሳትፎ ለዘላቂ የመንገድ መሰረተ ልማት!”በሚል መሪ ሀሳብ ከተለያዩ ክፍለ ከተሞች የተውጣጡ የህብረተሰብ ክፍሎች በከተማዋ በግንባታ ላይ የሚገኙ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

በመንገድ ጉብኝቱ ላይ ገለፃ ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ኢያሱ ሰለሞን በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የህብረተሰቡን የመንገድ መሠረተ-ልማት ጥያቄ የሚመልሱ፣ የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት የሚያሳልጡና ገፅታዋን እየቀየሩ የሚገኙ ተሸጋጋሪ ድልድዮችን ጨምሮ በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡

አቶ ኢያሱ አያይዘውም በተለያዩ ጊዜያት በከተማዋ ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ መንገዶች፤ የመዲናዋን የትራፊክ ፍሰት ከማቀላጠፍ ባሻገር፣ አዲስ አበባ ውብና ማራኪ ገፅታ እንድትላበስ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገቷም እንዲፋጠን ጉልህ አስተዋፅኦ እያበረከቱ አንደሚገኙ ተናግረዋል።

ይሁን እንጂ በመንገድ ሀብት አጠቃቀም ችግር ምክንያት በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ የከተማዋ መንገዶች በተደጋጋሚ ለብልሽት እየተጋለጡ እንደሚገኙ ጠቁመው፤ ህብረተሰቡ በየአካባቢው የሚገኘውን የመንገድ ሀብት በአግባቡ በመጠቀም፣ በመጠበቅና በመንከባከብ የጋራ ሀብቱን ከጉዳት እንዲከላከል አሳስበዋል።

በዕለቱ ጉብኝት ከተደረገባቸው የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል ቃሊቲ – ቱሉዲምቱ፣ ቃሊቲ አደባባይ – ቡልቡላ – ቂሊጦ፣ የቦሌ ሚካኤል ተሸጋጋሪ የትራፊክ ማሳለጫ ድልድይ፣ የቦሌ ኤርፖርት – ጎሮ እና የበሻሌ 40/60 የጋራ መኖሪያ ቤቶች የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ፕሮጀክቶች ይገኙበታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.