+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

የአቋራጭ መንገዶች ግንባታ ለትራፊክ መሳለጥ ወሳኝ ሚና አላቸው

አዲስ አበባ፣ ታህሳስ 23 ቀን 2016 ዓ.ም፡- በከተማችን አዲስ አበባ በርካታ አማራጭና አቋራጭ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ተገንብተው በመጠናቀቅ ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የመንገድ ፕሮጀክቶች ከዋና ዋና መንገዶች በተጨማሪ በከተማዋ እየተፈጠረ የሚገኘውን ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ችግር በመቀነስ ረገድ ሚናቸው የጎላ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች በለሥልጣንም በስራ ተቋራጮች ከሚያስገነባቸው ግዙፍ የመንገድ ፕሮጀክቶች በተጨማሪ በራሱ አቅም በከተማዋ በሁሉም ማዕዘናት በርካታ አቋራጭ መንገዶችን እየገነባ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት እየተገነቡ ከሚገኙ በርካታ አቋራጭ መንገዶች መካከል ከጀሞ አፍሪካ ህንፃ ጀርባ ጀምሮ እስከ ጀሞ መስታዎት ፋብሪካ ድረስ እየተገነባ የሚገኘው የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት አንዱ ነው፡፡

ይህ የመንገድ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 1.68 ኪሎ ሜትር ርዝመት እና 20 ሜትር የጎን ስፋት አለው፡፡ አሁን ላይ የፕሮጀክቱን የአስፋልት ስራ በጥቂት ቀናት ውስጥ ለማጠናቀቅ በምሽት ክፍለ ጊዜ ጭምር እየተሰራ የሚገኝ ሲሆን አጠቃላይ አፈፃፀሙም ከ85.5 በመቶ በላይ መድረስ ችሏል፡፡

ቀሪ የእግረኛ መንገድ ፣ የመንገድ ዳር መብራት ፖል ተከላ እና ተያያዥ ስራዎችንም በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ሙሉ በሙሉ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

የመንገድ ግንባታው ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በጀሞ አንድ አደባባይ ላይ እየተፈጠረ የሚገኘውን የትራፊክ መጭናነቅ በማቃለል በአካባቢው የተሻለ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.