+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

የየካ ጣፎ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የውስጥ ለውስጥ የመንገድ ግንባታ የስራ እንቅስቃሴ

አዲስ አበባ፣ ታህሣስ 22 ቀን 2016 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ምቹ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ እንዲኖራቸው ለማድረግ የውስጥ ለውስጥ መንገዶችን እየገነባ ይገኛል፡፡

ባለሥልጣን መስሪያቤቱ በጋራ መኖሪያ ቤቶች እየገነባቸው ከሚገኙ መንገዶች መካከል 3.9 ኪሎ ሜትር የአስፋልትና 6.8 ኪሎ ሜትር የኮብልስቶን መንገድ አካቶ እየተገነባ የሚገኘው የየካ ጣፎ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የውስጥ ለውስጥ መንገድ ፕሮጀክት ተጠቃሽ ነው፡፡

የዚህን የመንገድ ግንባታ እያከናወነ የሚገኘው የኢትዮጵያ ኮንስትራሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ሲሆን፣ አይዲኮን ደግሞ የማማከርና የቁጥጥር ስራውን እየተከታተለው ይገኛል፡፡ ለፕሮጀክቱ ማስፈፀሚያ ከ700 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተመድቦለታል፡፡

አሁን ላይ 1.6 ኪሎ ሜትር የሚሸፍነው የመንገዱ ክፍል የሰብ ቤዝ ስራ በመከናወን ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በቀሪው የፕሮጀክቱ ክፍል ላይ የአፈር ቁፋሮ፣ የፍሳሽ መስመር ትቦ ቀበራ፣ የድጋፍ ግንብ ግንባታ እና ሌሎች ተያያዥ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የወሰን ማስከበር ሥራው በተያዘለት ጊዜ ባለመጠናቀቁ ምክንያት የፕሮጀክቱ ግንባታ በታሰበው ፍጥነት እንዳይከናወን ተፅእኖ እያሳደረ ነው፡፡ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ አፈፃፀምም 25 በመቶ ላይ ይገኛል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ ግንባታ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ ለአገልግሎት ክፍት እንዲሆን የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በመንገድ ወሰን ውስጥ የሚገኙ ቀሪ የወሰን ማስከበር ስራዎችን በማከናወን ለፕሮጀክቱ በፍጥነት መጠናቀቅ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.