35 ኛውን የዓለም አቀፍ የፀረ-ኤድስ ቀን አስመልክቶ በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ውይይት ተካሄደ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 22 ቀን 2016ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አመራሮችና ሰራተኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ35ኛ ጊዜ በሀገራችን ለ34ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘውን የፀረ-ኤድስ ቀን ” የማህበረሰብ መሪነት ለላቀ ኤች አይቪ መከላከል” በሚል መሪ ቃል በውይይት እና በተለያዩ ዝግጅቶች አክብረዋል፡፡
በመርሀ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ቡድን መሪ ወይዘሪት ፀደንያ አበበ እንደገለፁት ኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት አሁንም በሀገራችን እንዳለ መረጃዎች እንደሚያመላክቱ ጠቁመዋል፡፡
ወይዘሪት ፀደንያ አያይዘውም ይሁን እንጂ በማህበረሱ ዘንድ በሽታው ከሀገራችን ጠፍቷል የሚል እሳቤ በመኖሩ ለቫይረሱ የሚሰጠው ጥንቃቄና ትኩረት በመቀነሱ አምራች የሆነውን የህብረተሰብ ክፍል እያጠቃ በመሆኑ ሁሉም ዜጋ እራሱን ከቫይረሱ መጠበቅ እንዳለበት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
ዕለቱን አስመልክቶ የውይይት መነሻ ሰነድ ያቀረቡት የባለስልጣኑ የሴቶችና ወጣቶች ጉዳይ ቡድን ሶሻል ወርክ ባለሙያ አቶ አበራ ሶሬሳ በበኩላቸው በሽታው በዓለም ላይ ማህበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ እና ስነልቦናዊ ቀውስ ያስከተለ በመሆኑ ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ተቀናጅቶ በመስራት ስርጭቱንና የሚያስከትለውን ተፅዕኖ ለመቀነስ መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በዝግጅቱ ላይ ከፀረ-ኤድስ ቀን በተጨማሪ የነጭ ሪቫን ፣የዓለም አቀፍ የህፃናት ቀን፣ እንዲሁም የአካል ጉዳተኞች ቀን በጥምረት ተከብሯል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity