+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዓለም አቀፍ የፀረ ሙስና ቀን አስመልክቶ በተዘጋጀ ሰነድ ላይ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አመራርና ሠራተኞች በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ20ኛ፣ በሀገራችን ደግሞ ለ19ኛ ጊዜ እየተከበረ የሚገኘውን ዓለም አቀፍ የፀረ-ሙስና ቀን “ሙስና የጋራ ጠላታችን ነው፤ በህብረት እንታገል” በሚል መሪ ሀሳብ በውይይት አክብረዋል፡፡

በመርሀ ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ እንደገለፁት ሙስና ስልጣንና ሀላፊነትን ያለአግባብ በመጠቀም ውስን የሆነውን የሀገር ሀብት ለራስ ጥቅም እንዲውል በማድረግ የሀገር ኢኮኖሚያዊ፣ፖለቲካዊና ማህበራዊ እድገት ላይ እያሳደረ የሚገኘው አሉታዊ ተፅዕኖ እጅግ ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም ሙስና እና ብልሹ አሰራር በሀገር እድገትና በዜጎች ኑሮ ላይ የሚያሳድረው ጉዳት ከፍተኛ በመሆኑ ከሙስና የፀዳች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መላ ሠራተኞች የበኩላቸውን ገንቢ ሚና ሊወጡ እንደሚገባ መዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ዕለቱን አስመልክቶ የውይይት የመነሻ ሰነድ ያቀረቡት በባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የስነ ምግባር መከታተያ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ደመቀች መንገሻ በበኩላቸው ሙስና ህግና ስርዓትን ተከትሎ ከመስራት ይልቅ ስልጣንና ኃላፊነትን መከታ በማድረግ የሚፈፀም ድንበር የለሽ ዓለም አቀፋዊ ወንጀል መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ወ/ሮ ደመቀች አያይዘውም ሙስና በዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ፣ በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ ከሚያሳድሩ ችግሮች መካከል ዋነኛው በመሆኑ፣ እንደ ሀገር ሙስናን ለመከላከል የሚደረገው ጥረት ውጤታማ እንዲሆን ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በቅንጅት ሊሰራ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ላይ የተሳተፉ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አመራርና ሰራተኞችም በተሰማሩበት የስራ መስክ ሙስና እና ብልሹ አሰራርን ለመከላከል የበኩላቸውን ሚና እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.