ቦሌ ሚካኤል ቤተክርስቲያን አካባቢ የሚገኝውን አደባባይ በማንሳት በትራፊክ መብራት የመተካት ሥራ ተጀመረ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 21 ቀን 2016 ዓ.ም፤ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በከተማዋ የመንገድ መጋጠሚያ ስፍራዎች የሚታየውን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ለመፍታት እንደየ አካባቢዎቹ ተጨባጭ ሁኔታ የተለያዩ የመፍትሄ አማራጮችን ተግባራዊ በማድረግ የትራፊክ ፍሰት ማሻሻያ ሥራዎችን እያከናወነ ይገኛል፡፡
አሁን ላይ አደባባይ በማንሳት በትራፊክ መብራት የመቀየር ሥራ እየተከናወነ ከሚገኝባቸው አካባቢዎች መካከል ከቦሌ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ጀርባ የሚገኘው አደባባይ ይገኝበታል፡፡
ትናንት ምሽት የተጀመረው ይህ የትራፊክ ፍሰት ማሻሻያ ስራ ከቅሊንጦ – ቡልቡላ – ቦሌ ሚካኤል የመንገድ መረብ ጋር ተሳስሮ በአካባቢው እየጨመረ የመጣውን የትራፊክ ጫና በአግባቡና በፍጥነት ለማስተናገድ የሚያግዝ ነው፡፡
ቀደም ሲል በቦሌ ሚካኤል የመንገድ መጋጠሚያ ላይ ይከሰት የነበረው የትራፊክ መጨናነቅ ችግር በተገነባው ግዙፍ የትራፊክ ማሳለጫ ተሸጋጋሪ ድልድይ አማካኝነት የተፈታ ቢሆንም፤ ከቦሌ ሚካኤል ቤተክርስቲያን ጀርባ በሚገኘው አደባባይ ላይ እየተፈጠረ ባለው የትራፊክ መጨናነቅ ሳቢያ የትራፊክ ፍሰት ማሻሻያ ስራውን ማከናወን አስፈልጓል፡፡
ባለሥልጣን መስሪያቤቱ የትራፊክ ፍሰት ማሻሻያ ስራውን የትራፊክ እንቅስቃሴ በማይበዛባቸው ክፍለ ጊዜያት በመስራት በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ ሙሉ በሙሉ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እየሰራ የሚገኝ መሆኑን እየገለፀ፣ የመንገዱ ተጠቃሚዎችም አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ባለሥልጣን መስሪያቤቱ ያሳስባል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity