መንገድን በተመለከተ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ለምክር ቤት አባላት ከተናገሩት
አሁን ባለው ሁኔታ የአዲስ አበባ መንገድ ሽፋን ከተማዋን የሚመጥን አይደለም፤ ይህንን መነሻ በማድረግ የመንገድ የመሰረተ ልማቶች በታቀደላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡
በመጀመርያው ሩብ ዓመት ከመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ፕሮጀክቶች ጋር በተያያዘ አጠቃላይ ርዝመታቸው 20 ኪሎሜትር እና እስከ 43 ሜትር የጎን ስፋት ያላቸው በአጠቃላይ ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገባቸው ዘጠኝ የመንገድ ስራ ፕሮጀክቶች ለትራፊክ ክፍት የሆኑ ሲሆን በሌላ በኩል ባለፉት ሶስት ወራት ውስጥ 277 ኪሜ የመንገድ ግንባታ እና ጥገና ስራዎችን ለማከናወን ታቅዶ 308 ኪሜ ማሳካት ተችሏል፡፡
የህብረተሰቡ ከፍተኛ የመልካም አስተዳደር ምንጭ ሆኖ የቆየው የቃሊቲ ቱለዱምቱ የመንገድ ስራ ፕሮጀክት በዚሁ ሩብ ዓመት በሁለቱም አቅጣጫ ለትራፊክ ክፍት ማድረግ በመቻሉ የመልካም አስተዳደር ችግሩን ከመቅረፍ በተጨማሪ በትራንስፖርት ላይ ይባክን የነበረውን ጊዜ በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ ተችሏል፡፡ ፕሮጀክቱ በአሁኑ ወቅት 78% አፈጻጸም ያለው ሲሆን በቀጣይ 3 ወራት ውስጥ ይጠናቀቃል።
በሌላ በኩል በስፋቱም በርዝመቱም እጅግ በጣም ግዙፍ የድልድይ ግንባታ ስራን ያካተተው አጠቃላይ ርዝመቱ 10.5 ኪ. ሜ ርዝመት ያለው የቃሊቲ ቂሊንጦ መንገድ ግንባታ በዚሁ ሩብ ዓመት የሪፖርት ጊዜ ውስጥ በከፊል ክፍት የተደረገ ሲሆን በአሁኑ ወቅት 90 % አፈፃፀም ላይ ማድረስ ተችሏል፡፡