+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

መንገድ የሁላችንም የጋራ ሀብት ነው፤ ከህገ ወጥ ተግባራት ልንጠብቅ ይገባል!

አዲስ አበባ፣ ህዳር 10 ቀን 2016ዓ.ም፡-አዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የከተማዋን የመንገድ ሽፋን ለማሳደግና የትራፊክ ፍሰቱን ይበልጥ ምቹ ለማድረግ በየዓመቱ በከፍተኛ በጀት የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎችን በማከናወን የከተማችንን ነዋሪዎች ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየሠራ ይገኛል።

ይሁን እንጂ በመንገድ ሀብት ላይ ባለው የአጠቃቀም ጉድለትና ኃላፊነት በጎደለው ህገወጥ ተግባራት ምክንያት በመንገድ ሀብታችን ላይ በየጊዜው እየደረሰ ያለው ጉዳት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል።

በከተማዋ የአስፋልት መንገድ ላይ በህገ-ወጥ መንገድ የኮንክሪት ግንብ በመገንባት ለመኪና መግቢያ መውጫነት መጠቀም በእግረኛ መንገዶች ላይ መኪና በማቆም እንዲሁም በእግረኛ መንገድ ላይ መኪና አቁሞ እቃ በመጫን እና በማውረድ የመንገድ ሀብት ላይ ከፍተኛ ጉዳት እየደረሰ ይገኛል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በሚፈፀሙ ህገ-ወጥ ተግባራት ምክንያት የተገነቡ የድሬኔጅ መስመሮች ለጉዳት በመጋለጣቸው የዝናብ ውሃ ወደ ድሬኔጅ መስመር በቀጥታ እንዳይገባ ስለሚሆን የአስፋልት መንገድ በጎርፍ እንዲጥለቀለቅ በማድረግ መንገዱ ሊሰጠው ከሚገባው አገልግሎት ጊዜ በፊት እንዲበላሽ እያደረገ ነው፡፡

ከዚህ ባለፈ በዝናብ ወቅት በሚከሰት ጎርፍ ሳቢያ በአካባቢው በሚኖሩ ህብረተሰብ ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጫና በመፍጠርና በትራፊክ እንቅስቃሴው ላይ አሉታዊ ጫና እያሳደረ ይገኛል፡፡

ለአብነትም ከለቡ እስከ ቫርኔሮ በሚወስደው መንገድ ላይ በህገ-ወጥ ግለሰቦች የተገነባ የኮንክሪት ግንብ በባለስልጣኑ የደቡብ አዲስ አበባ የመንገድ ሀብት አስተዳደር ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በግብረ-ሃይል እንዲፈርስ ተድርጓል፡፡

እነዚህንና መሰል ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል ባለስልጣኑ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የእርምት እርምጃ እየወሰደ ይገኛል፡፡

ለመንገዶች ብልሽት ምክንያት የሆኑ ህገወጥ ተግባራትን በመከላከል ለታለመለት አላማ እንዲውሉ ለማድረግ ሁላችንም ኃላፊነታችንን በጋራ እንወጣ ሲል ባለስልጣኑ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.