+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ባለስልጣኑ ለአቅመ ደካማ ነዋሪዎች የገነባውን መኖርያ ቤት አስረከበ

አዲስ አበባ፣ ህዳር 8 ቀን 2016 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 በተለምዶ 30 ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በ2 ሚሊዮን ብር ወጪ ለአቅመ ደካማ ነዋሪዎች የገነባውን ባለ አራት ክፍል መኖሪያ ቤት በአጭር ጊዜ ውስጥ አጠናቆ በትላንትናው ዕለት ለተጠቃሚዎች አስረክቧል፡፡

በርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ብልፅግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፌ አቶ አደፍርስ ኮራ እንደገለፁት፤ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የከተማዋን የመንገድ መሠረተ ልማት ከመገንባት በተጨማሪ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች እየተሣተፈ የህብረተሰቡን ማህበራዊ ችግሮች ለማቃለል የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

አቶ አደፍርስ አያይዘውም፤ ባለሥልጣን መስሪያቤቱ ቀደም ሲልም በክፍለ ከተማው ውስጥ በርካታ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ የጋራ መኖሪያ ህንፃ ገንብቶ ያስረከበ መሆኑን አውስተው፣ ይህንኑ ሰናይ ተግባር አጠናክሮ በመቀጠል በአጭር ጊዜ ይህንን ቤት ገንብቶ ለተጠቃሚዎች ለማስረከብ በመቻሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኢያሱ ሰሎሞን በበኩላቸው፤ ባለሥልጣን መስሪያቤቱ በአዋጅ ከተሰጠው መደበኛ ተልዕኮው በተጨማሪ በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መስኮች ላይ በመሳተፍ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ጠቅሰው፣ ቀደም ሲልም በተለያዩ ክፍለ ከተሞች 31 አቅመ ደካማ ወገኖችን ተጠቃሚ ያደረጉ የቤቶች እድሳት ማከናወኑን አውስተዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የባለሥልጣን መስሪያቤቱ ሠራተኞች በቋሚነት ለሚደግፋቸው 50 ህፃናት ድጋፍ እና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ምድረ ግቢና የመቃረቢያ መንገዶች ግንባታ እያከናወነ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በቀጣይም መሰል የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራትን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አቶ ኢያሱ አያይዘው ገልፀዋል፡፡

የቤት ቁልፍ የተበረከተለትና በባለሥልጣነ መስሪያቤቱ ሰራተኞች በቋሚነት ድጋፍ ከሚደረግላቸው 50 ህፃናት መካከል አንዱ የሆነው ህፃን ኢዩኤል ወርቁ በበኩሉ፤ ቀደም ሲል እሱና ቤተሰቦቹ የሚኖሩበት ቤት በጣም የተጎዳ እና በክረምት ወቅት ጎርፍ ይገባበት እንደነበር እና ለመኖርም ሆነ ለማጥናት ምቹ እንዳልነበር ጠቅሶ፣ አሁን ላይ የዘመናዊ ቤት ባለቤት በመሆናቸው የተሰማውን ደስታ ገልጿል፡፡

በሌላም በኩል የህፃኑ አሳዳጊ ወይዘሪት ቀለምወርቅ ወርቁ በበኩላቸው፤ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ቀደም ሲል በመኖሪያ ቤታችን የነበረውን ምቹ ያልሆነ ሁኔታ ለመቀየር እና ችግራችንን በዘላቂነት ለመፍታት በአጭር ጊዜ ውስጥ ቤቱን ገንብቶ በማጠናቀቅ ስለአስረከባቸው ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.