የግንባታ ግብዓቶችን በእግረኛና በተሽከርካሪ መንገዶች ላይ በማራገፍ መንገድ በዘጉ አካላት ላይ የማስተካከያ እርምጃ ተወሰደ
አዲስ አበባ፣ ህዳር 6 ቀን 2016 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች በተገነቡ የእግረኛ እና የተሸከርካሪ መንገዶች ላይ የግንባታ ግብዓቶችን በማራገፍ መንገድ በዘጉ አካላት ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ ተደርጓል፡፡
በመዲናዋ መንገዶች ላይ እየተፈፀመ ያለው ህገ-ወጥ ተግባር በከፍተኛ ወጪ የተገነቡትን የመንገድ ሀብቶች ለከፍተኛ ጉዳት እያጋለጠ ከመሆኑም ባሻገር፣ የትራፊክ እንቅስቃሴውን በማስተጓጎል ህብረተሰቡን ለትራፊክ አደጋ እያጋለጠ ይገኛል፡፡
በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ለቡ አካባቢ በእግረኛና በኮብል መንገድ ላይ የግንባታ ግብዓቶች ያስቀመጡ ግለሰቦች ከህገ-ወጥ ድርጊታቸው እንዲታረሙ በተደጋጋሚ የቃልና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው ቢሆንም ከድርጊታቸው ሊቆጠቡ ባለመቻላቸው፤ የደቡብ አዲስ አበባ የመንገድ ሀብት አስተዳደር ከትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ፣ ከወረዳው ፖሊስ እና ደንብ ማስከበር ጋር በመቀናጀት በእግረኛና በኮብል መንገዱ ላይ የተከማቸው አሸዋና ጠጠር እንዲነሳ አድርጓል፡፡
በሁሉም የከተማዋ ክፍሎች በመንገድ ላይ የግንባታ ግብዓትና ተረፈ ምርቶችን ያከማቹ፣ በመንገድ ወሰን ውስጥ የተሸከርካሪ አካላት ጥገና ሥራ የሚያከናውኑ እና በእግረኛ መንገድ ላይ መኪና የሚያቆሙ አካላት ከህገ-ወጥ ድርጊታቸው እንዲታቀቡ ባለሥልጣን መስሪያቤቱ በአፅንኦት እያሳሰበ፤ ማሳሰቢያውን ተግባራዊ በማያደርጉት ላይ የተጀመረው የእርምት እርምጃ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ይገልፃል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity