የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከፍተኛ አመራሮች እና የምክር ቤት አባላት የተለያዩ ፕሮጀክቶችን ጎብኝተዋል::
ከቻይናው ኤግዚም ባንክ ይገኛል የተባለው ብድር ባለመገኘቱ ለረዥም ጊዜያት የህዝብ ቅሬታ ምንጭ የነበረው አሁን በከተማው አቅምና በጀት በመገንባት ላይ የሚገኘው ግዙፉ የቡልቡላ እና አቃቂ ወንዞችን ተሻግሮ ቂሊንጦ ሁለተኛ ቀለበት ፣ ከቃሊቲ አደባባይ እስከ ቱሉ ዲምቱ አደባባይ ያለው 10.5 ኪ.ሜ ርዝመት የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታና የመንገዱ አንድ አካል የሆነውና 325 ሜትር ርዝመት ያለው የማሳለጫ ድልድይ የከተማዋ አማራጭ የመግቢያና መውጫ ኮሪደርን ጎብኝተዋል::
በጉብኝቱ አፈ-ጉባኤ ክቡር አቶ ታገሰ ጫፎ ታላቅ ራዕይ እና ሀሳብን ሰንቀው የሚገነቡ የልማት ፕሮጀክቶች ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ እና ገፅታ ግንባታ ድርሻቸው የላቀ መሆኑን ጠቅሰው ሀገሪቱ ከውጪና ከውስጥ በገጠሟት ተግዳሮቶች ውስጥ ሆና የጫካ ፕሮጀክትን ጨምሮ እነዚህን ፕሮጀክቶች መገንባት መቻሏ ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቁመዋል።
የምክር ቤት አባላቱ ከጎበኟቸው ፕሮጀክቶች መካከል የጫካ ፕሮጀክት አንዱ ሲሆን ፕሮጀክቱ ትልቅ ራዕይ ተይዞ ባይሰራ እስከ ዛሬ ድረስ ያለምንም ለውጥ ጫካ ብቻ ሆኖ ይቀር ነበር ያሉት አፈ-ጉባኤ አቶ ታገሰ ለዚህ ስኬት የሀሳቡ አፍላቂ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አሕመድ(ዶ/ር)፣ የስራ ባልደረቦቻቸው እና የፕሮጀክቱ ሰራተኞች በሙሉ ሊደነቁና ሊመሰገኑ ይገባልም ብለዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ኃላፊ እና የካቢኔ ጉዳዮች ሚኒስትር ወ/ሮ አለምፀሀይ ጳውሎስ በበኩላቸው የጫካ ፕሮጀክትን ጨምሮ የተገነቡት የመንገድ፣ የድልድይ፣ የዋና እና የውስጥ ለውስጥ የመንገድና የትላልቅ ድልድዮች ግንባታ የሀገሪቱን ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ፣ ለዜጎች የስራ እድልን የፈጠሩ፣ ከተማዋን ተጨማሪ ውበት ያላበሱ፣ የትራፊክ መጨናነቅን ያስቀሩ፣ ዜጎችን ከእንግልትና ከተጨማሪ የትራንስፖርት ወጪ የታደጉ፣ ፍትሀዊ እና ሁሉን አካታች መሆናቸውን አብራርተዋል።
የአቃቂ ኢንተርናሽናል ስታዲየም፣ የአይነ ስውራን እና የሴቶች ማገገሚያ ማዕከላት ግንባታቸው በመጠናቀቅ ላይ መሆኑንም ወ/ሮ አለምፀሀይ ጳውሎስ ጨምረው ገልፀዋል::