+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ቋሚ ኮሚቴው ለመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች ማነቆ የሆኑ ችግሮች እንዲፈቱ የበኩሉን እገዛ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አረጋገጠ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 28 ቀን 2016 ዓ.ም፡- በአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የመሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ አባላት በመንገድ መሰረተ ልማት ስራዎች ላይ እያጋጠሙ የሚገኙ ችግሮችን ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት የአየር ጤና – ወለቴ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት የወሰን ማስከበር ሥራ የሚገኝበትን ደረጃ ተዘዋውረው የተመለከቱ ሲሆን፣ በመሬት ውስጥ የተቀበሩ የኤሌክትሪክ መስመሮች፣ ያልተነሱ የግል እና የመንግስት ቤቶች በመንገድ ፕሮጀክቱ የወሰን ክልል ውስጥ መኖራቸውን ለማየት ችለዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ክንፈ አዲስ የአየር ጤና ወለቴ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ለከተማዋ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገት መሳለጥ ከፍተኛ ድርሻ ያለው መሆኑን ጠቁመው፣ ከወሰን ማስከበር ጋር በተያያዘ ያጋጠሙ ችግሮችን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንዲፈቱ የሚመለከታቸውን ባለድርሻ አካላት በማነጋገር ፈጣን ምላሽ እንዲሰጥበት ቋሚ ኮሚቴው የሚሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የተከበሩ አቶ ክንፈ አክለውም ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዙ ችግሮችን ለመፍታት ከቅንጅታዊ አሰራር ጎን ለጎን በቀጣይ ትኩረት ተሰጥቶት እንዲሰራ ለማድረግ አስገዳጅ የአሰራር ስርዓት መዘርጋት እንዳለበትም አመልክተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ በበኩላቸው በመሬት ውስጥ በተቀበሩ የዩቲሊቲ መስመሮች እና በሌሎች የወሰን ማስከበር ችግሮች ምክንያት የአየር ጤና ወለቴ የመንገድ ፕሮጀክትን በታቀደው የግንባታ ጊዜ ለማስጀመር እንዳልተቻለ ገልፀዋል፡፡

ኢንጂነር ሞገስ አያይዘውም ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ለከተማዋ ካለው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በተጨማሪ የሀገራችን ምዕራባዊ ክፍል የመግቢያና የመውጫ ኮሪዶር በመሆኑ የወሰን ማስከበር ስራው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ወደ ሙሉ የግንባታ ትግበራ እንዲገባ ሁሉም ባለድርሻ አካላት የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.