አካታች የመንገድ መሠረተ-ልማት ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያሻሽል የማንዋል ጥናት እየተከናወነ ነው
የማንዋል ዝግጅቱን ለማዳበር የሚያስችል የባለድርሻ አካላት የውይይት መድረክም መካሄድ ጀምሯል፡፡
ጥቅምት 16 ቀን 2016 ዓ.ም አዲስ አበባ፡-የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ከዓለም ባንክ ባገኘው 94.8 ሚሊየን ብር ድጋፍ ዳር አልሐንዳስ አማካሪዎች ከተባለ ዓለም አቀፍ ድርጅት ጋር በተደረገ ስምምነት አካታች የመንገድ መሠረተ-ልማት መገንባት የሚያስችል የ 28 ማንዋሎች ዝግጅት በመካሄድ ላይ ነው፡፡
በውይይት መድረኩ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሞገስ ጥበቡ እንደገለፁት አሁን ላይ የመጡ አዳዲስ አሰራሮችና ዘመኑ ያፈራቸውን ቴክኖሎጂዎች ጥቅም ላይ የሚያውል ሁሉን አካታች የመንገድ መሠረተ ልማት ለመገንባት የሚያስችል የማንዋል ጥናት እየተከናነ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡
ኢንጅነር ሞገስ አያይዘውም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነች ከተማ ለመፍጠር እየተከናወነ ባለው ሁሉን አቀፍ እንቅስቃሴ ውስጥ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተደደር በመንገድ መሠረተ-ልማት ዘርፍ ለማሳካት ያለመውን የረጅም ጊዜ ዕቅድ እውን ለማድረግ በየመስኩ የተሸሻሉ የማስተግበሪያ ማንዋሎች እንደሚያስፈልጉ አብራርተዋል፡፡
በጥናት ላይ የሚገኙት ማንዋሎች ተጠናቀውና ፀድቀው ተግባር ላይ ሲውሉ፣ በከተማዋ በተሻለ ደረጃ የትራፊክ ፍሰትና የመንገድ ደህንነትን ለማስጠበቅ እገዛ የሚያደርጉ ከመሆኑም ባሻገር፣ መንገዶች ለታለመላቸው ዓላማ እንዲውሉ እና ሰው ተኮር ለሆኑ የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት የላቀ የመንገድ መሰረተ-ልማት ለማቅረብ ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡
ከዚህም በተጨማሪ በመንገድ ግንባታ ሂደት ያላአግባብ የሚባክነውን ጊዜ እና የግንባታ ወጪ በከፍተኛ ሁኔታ ለመቀነስ አስተዋፅኦ ያላቸው ከመሆኑም ሌላ፣ ደረጃቸውን የጠበቁ እና የከተማዋን ገጽታ በበለጠ ሁኔታ የሚቀይሩ ዘመናዊ መንገዶችን ለመንባት እገዛ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል፡፡
አውደ ጥናቱ በተለያዩ የማንዋል ዝግጅቶች ላይ ትኩረት አድርጎ ለሰባት ተከታታይ ቀናት የሚቀጥል ሲሆን፣ አሁን በሥራ ላይ ያሉ የመንገድ መሰረተ-ልማት ማንዋሎችን ነባራዊ ሁኔታ በመዳሰስ እና የአሰራር ክፍተቶችን በመለየት አዳዲስ አሰራሮችን አካቶ እንደሚቀርብ ይጠበቃል፡፡
በአውደ ጥናቱ ላይ የስራ ተቋራጮች፣ አማካሪ ድርጅቶች፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ ከኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር፣ ከኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን፣ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ዲዛይን እና ቁጥጥር ሥራዎች ኮርፖሬሽን እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት የተውጣጡ ተሣታፊዎች እየተካፈሉበት ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity