የመንገድ ጥገና ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል
በተለያዩ ምክንያቶች ጉዳት የደረሰባቸው የድሬኔጅ መስመሮች እና የማንሆል ክዳኖችም በመታደስ ላይ ናቸው
ጥቅምት 11 ቀን 2016 ዓ.ም፤ አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን፤ በበጀት ዓመቱ ለማከናወን በዕቅድ ከያዛቸው ልዩ ልዩ የመንገድ ጥገና ሥራዎች መካከል፣ በአጠቃቀምና እንክብካቤ ጉድለት ሳቢያ ጉዳት የደረሰባቸውን የድሬኔጅ መስመሮች እና ማንሆል ክዳኖችን መጠገን ይገኝበታል፡፡
በከተማዋ ጎዳናዎች ዳርቻ በተዘረጉ የመንገድ ዳር ውሃ መፋሰሻ መስመሮች እና በማንሆል ክዳኖች ላይ በተደጋጋሚ በሚፈጸም ህገ-ወጥ ተግባር ምክንያት፣ የከተማዋ መንገዶች ለህብረተሰቡ ተገቢውን አገልግሎት እንዳይሰጡ እንቅፋት ሆኖ ቆይቷል፡፡
ባለሥልጣን መስሪያቤቱ፤ የከተማዋ መንገዶች ለብልሽት እንዲጋለጡ ዋነኛ ምክንያት እየሆነ የሚገኘውን የድሬኔጅ መስመር ችግር ለመፍታት፣ በደረቅ ቆሻሻ የተደፈኑ የመንገድ ዳር ውሃ መውረጃ መስመሮችን እና በተለያየ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን የማንሆል ክዳኖች በመጠገንና በመቀየር ላይ ይገኛል፡፡
የድሬኔጅ መስመር ጥገና እና የማንሆል ክዳን መቀየር ስራ ከተከናወነባቸው አካባቢዎች መካከ፤ ጎማ ተራ፣ ጉራራ አካባቢ፣ በላይ ዘለቀ ት/ቤት አካባቢ፣ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት አካባቢ፣ ላፍቶ ታክሲ ተርሚናል፣ ማንጎ ጨፌ አካባቢ እና ጭድ ተራ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች በመኪና ግጭት፣ በስርቆት እና በሌሎች ምክንያቶች ክፍት የሆኑ ማንሆሎችን የመጠገን እና የመክደን ስራ በስፋት ተከናውኗል፡፡
በከተማዋ ጎዳናዎች ዳርቻ የተዘረጉት የመንገድ ዳር ውሃ መፋሰሻ መስመሮች፣ የዝናብ ውሃን ወደ ተፈጥሮ የውሃ መፋሰሻ መስመሮች በማስተላለፍ የከተማዋ መንገዶች ደህንነታቸው ተጠብቆ ለረጅም ዓመታት አገልግሎት እንዲሰጡ ከፍተኛ አስተዋፅኦ የሚያበረክቱ እጅግ አስፈላጊ የመንገድ አካላት ናቸው፡፡
በመሆኑም ሕብረተሰቡ ደረቅ ቆሻሻዎችን ወደ ድሬኔጅ መስመሮችና ማንሆሎች ባለመጣል ለመንገድ ሃብቱ ደህንነት መጠበቅ የበኩሉን የባለቤትነት ድርሻ በንቃት እንዲወጣ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity