+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ከመላው የሀገሪቱ ክፍሎች የተውጣጡ አመራሮች የአዲስ አበባ ከተማን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 5 ቀን 2016 ዓ.ም፡- ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የተውጣጡ ከ1 ሺህ በላይ የሆኑ ከፍተኛ አመራሮች የከተማዋን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

ለአመራሮቹ ገለፃ ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ፤ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የህብረተሰቡን የመንገድ መሰረተ-ልማት ጥያቄ የሚመልሱ እና የከተማዋን ገፅታ እየቀየሩ የሚገኙ ዘመናዊ የመንገዶች በተለያዩ የከተማዋ ማዕዘናት እየተገነቡ እንደሚገኙ አስረድተዋል፡፡

ኢንጂነር ሞገስ አክለውም በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ለመፍታት ከ2.8 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 2.3 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍኑ 6 የትራፊክ ማሳለጫ ተሸጋጋሪ ድልድዮች እየተገነቡ መሆናቸውን ለጉብኝቱ ተሳታፊዎች ገልፀዋል፡፡

ባለፉት 5 የለውጥ ዓመታት በተካሄደው መጠነ ሰፊ የመንገድ ግንባታ ሥራ የከተማዋ የመንገድ ኔትዎርክ እያደገ መምጣቱን ጠቁመው፤ በከተማዋ እየተከናወነ የሚገኘውን የመሰረተ-ልማት ተደራሽነት ማስፋፋት ተከትሎ የህብረተሰቡ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት እየጨመረ መምጣቱን ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለሞተር አልባ ትራንስፖርት ልዩ ትኩረት በመስጠት 16 ኪሎ ሜትር ርዝመት የሚሸፍን የፔዳል ሳይክል መንገድ እና ከ150 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት የሚሸፍኑ የእግረኛ መንገዶችን ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱን ዋና ዳይሬክተሩ አውስተዋል፡፡

የጉብኝቱ ተሳታፊዎች ከተመለከቷቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል፤ ከ787 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ተገንብቶ በትናንትናው ዕለት በይፋ የተመረቀው የቦሌ ሚካኤል የትራፊክ ማሳለጫ ተሸጋጋሪ ድልድይ ይገኝበታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.