+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ከ 2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገነቡ 9 የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በይፋ ተመረቁ

አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 4 ቀን 2016 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ከ2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ በተለያዩ የከተማዋ አካባቢዎች የተገነቡ 9 የመንገድ ፕሮጀክቶችን የፌዴራልና የከተማዋ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በዛሬው ዕለት በይፋ አስመርቋል፡፡

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አበቤ የከተማ መስተዳድሩ ዘርፈ ብዙ አስተዋፅኦ የሚያበረክተውን የመንገድ መሰረተ ልማት ልዩ ትኩረት በመስጠት ከፍተኛ በጀት መድቦ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ግንባታቸው ተጠናቆ ለምረቃ የበቁት የመንገድ ፕሮጀክቶች የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት ከማሳለጣቸውም ባሻገር፤ የጉዞ ጊዜንና ወጪን በመቀነስ፣ የከተማውን ገፅታ በመቀየር፣ የስራ እድል በመፍጠር፣ የመንገድ ደህንነትን በማረጋገጥ እንዲሁም የከተማውን የማህበራዊ መስተጋብር በማሻሻልና ኢኮኖሚውን በማነቃቃት ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱም ክብርት ከንቲባዋ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ከንቲባዋ አያይዘውም የመንገድ ፕሮጀክቶቹ ጀምሮ የመጨረስ፣ በገባነው ቃል መሰረት የማገልገል እና የህዝባችንን ጥያቄዎች በተጨባጭ እየመለስን መሆናችንን የሚያሳዩ ናቸው ብለዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ በበኩላቸው ከ20 ኪሎሜትር በላይ ርዝመት እና እስከ 43 ሜትር ስፋት ያላቸው ዘጠኝ የመንገድ ፕሮጀክቶች ለምረቃ መብቃታቸውን ገልፀዋል፡፡

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ዛሬ የተመረቁት መንገዶች ከዲዛይን ዝግጅታቸው ጀምሮ እስከ ግንባታ ፍፃሜ ድረስ በሀገር በቀል ባለሙያዎች እና ሀገራችን ባፈራችው ሀብት የተገነቡ በመሆናቸው ሀገራችን የጀመረችውን የከፍታ ጉዞ ማሳያ ተደርገው ሊወሰዱ የሚችሉ ናቸው ብለዋል፡፡

በዛሬው ዕለት ለምረቃ ከበቁት የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል ግዙፉ የቦሌ ሚካኤል ማሳለጫ ድልድይ፣ የአራራት ሆቴል – ኮተቤ ካራ እና የቄራ ከብት በረት -ጎፋ መብራት ኃይል ፣የቀጨኔ – ቁስቋም የመንገድ ፕሮጀክት፣ የኮተቤ አማኑኤል -ኮተቤ እና በጋራ መኖሪያ ቤቶች አካባቢ የተገነቡት የአያት መሪ ሳይት 4፣ ቦሌ አያት ሳይት 2 የመንገድ ለአብነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.