በመንገድ ግንባታ ስራዎች የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቅንጅት ለመፍታት የሚያስችል የትስስር ሰነድ ተፈረመ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 30 ቀን 2016 ዓ.ም፡- ‹‹ የባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ተሳትፎ ለዘላቂ የመንገድ መሰረተ ልማት›› በሚል መሪ ሀሳብ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በመንገድ ግንባታ ስራዎች ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በቅንጅት ለመፍታት ከመንገድ መሰረተ ልማት ባለድርሻ አካላት ጋር የትስስር ሰነድ የፊርማ ስነ-ስርዓት በዛሬው ዕለት አከናውኗል፡፡
መርሀ ግብሩን በንግግር የከፈቱት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሞገስ ጥበቡ ባለስልጣኑ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የህብረተሰቡን የመንገድ መሠረተ-ልማት ጥያቄ የሚመልሱ እና በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ለመፍታት 6 የትራፊክ ማሳለጫ ተሸጋጋሪ ድልድዮች በከፍተኛ መዋለ ነዋይ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች እየተገነቡ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
በ2015 በጀት ዓመት ከ1ሺ ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ግንባታ እና ጥገና ስራዎች ማከናወን መቻሉን አስታውሰው፤ ለዚህም ስኬት ባለድርሻ አካላት ለአበረከቱት አስተዋፆ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በተያዘው በጀት ዓመትም ከ9 መቶ ኪሎ ሜትር በላይ የግንባታ እና የጥገና ስራዎችን ለማከናወን አቅዶ ወደ ስራ መግባቱን ጠቁመው ፤ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቁ የወሰን ማስከበር ስራ ወሳኝ በመሆኑ ክፍለ ከተሞች እና የሌሎች ባለድርሻ አካላት የጀመሩትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ አሳስበዋል፡፡
በመንገድ ሀብት አጠቃቀም ችግር በከተማዋ የሚገነቡ መንገዶች ረጅም ጊዜ አገልግሎት ሳይሰጡ እየተበላሹ እንደሚገኙ ገልፀው፤ በከፍተኛ ወጪ የተገነቡ የመንገድ መሰረተ ልማቶች ለታለመላቸው ዓላማ ብቻ እንዲውሉ በማድረግ በኩል የባለድርሻ አካላት ሚና ከፍ ያለ መሆኑን ጠቁመዋል።
የውይይት መነሻ ሰነድ ያቀረቡት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የእቅድ፣ በጀትና ስትራቴጅክ ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ አብነት ኤርጌንዶ በበኩላቸው፤ ባለስጣን መስሪያ ቤቱ ከመንገድ መሰረት ልማት ጋር በተያይዘ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በቅንጅት ለመፍታት የትስስር ሰነዱ አስፈላጊ መሆኑ ገልፀዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች በበኩላቸው ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የከተማዋን የመንገድ ሽፋን ከጊዜ ወደ ጊዜ ለማሳደግ እያደረገ ያለውን ጥረት አድንቀው፣ የትስስር ሰነዱን መነሻ በማድረግ በቅንጅት ለመስራት እናየበኩላቸውን የባለድርሻነት ሚና ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አረጋግጠዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity