+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

በኤምፔሪያል የትራፊክ ማሳለጫ ተሸጋጋሪ ድልድይ ግንባታ ፕሮጀክት የተደራቢ አስፋልት ማልበስ ሥራ እየተከናወነ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 28 ቀን 2016 ዓ.ም፡- በውስጠኛው የቀለበት መንገድ ላይ እየተገነቡ ከሚገኙ የትራፊክ ማሳለጫ ተሸጋጋሪ ድልድይ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ በሆነው በኤምፔሪያል የትራፊክ ማሳለጫ ተሸጋጋሪ ድልድይ የመንገድ ፕሮጀክት የተደራቢ አስፋልት ማልበስ ሥራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡

በአሁኑ ወቅት የማሳለጫ ድልድዩን የመቃረቢያ መንገዶች የመጨረሻ ደረጃ አስፋልት የማልበስ ስራ እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን፣ አሁን ላይ የፕሮጄክቱ አጠቃላይ የፊዚካል አፈፃፀም 88.7 በመቶ ደርሷል፡፡

ከባለፈው ዓመት የበልግ ወቅት ጀምሮ እስከ ክረምቱ ወቅት ማጠናቀቂያ ድረስ የዘለቀው ረጂም የዝናብ ጊዜ በከተማዋ የመንገድ ግንባታና ጥገና እንቅስቃሴዎች ላይ ተፅእኖ ያሳደረ ቢሆንም፣ በተደረገው ከፍተኛ ርብርብ የተሸጋጋሪ ድልድዩ ግንባታ ተጠናቆ፣ ዋናው ክረምት ከመግባቱ አስቀድሞ መንገዱ ለትራፊክ አገልግሎት ክፍት መደረጉ ይታወሳል፡፡

በቀጣዮቹ ጥቂት ቀናት የፕሮጄክቱን ቀሪ አስፋልት ማንጠፍ ስራ ሙሉ በሙሉ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ሲሆን፣ የመንገድ ዳር መብራት ተከላ እና የእግረኛ መንገድ ስራም በተከታታይ የሚከናወን ይሆናል፡፡

የኤምፔሪያል የትራፊክ ማሳለጫ ተሸጋጋሪ ድልድይ ግንባታ ፕሮጀክት የመቃረቢያ መንገዶችን ጨምሮ በአጠቃላይ 1.8 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 40 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሲሆን፣ ለግንባታው ማስፈፀሚያ ከ714.8 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት ተይዞለታል፡፡

ፕሮጀክቱ በቻይና ፈርስት ሃይ ዌይ ኢንጂነሪንግ እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን የማማከርና የቁጥጥር ስራውን ደግሞ ስታዲያ እና ጂ ኤንድ ዋይ ኢንጂነሪንግ የተባሉ አማካሪ ድርጅቶች በጋራ እየተከታተሉት ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.