አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከመስከረም 24 ጀምሮ ልዩ ልዩ ዓለም አቀፍ፣ አህጉር አቀፍ እና አገር አቀፍ መድረኮችን ያስተናግዳል:- ወ/ሮ እናትአለም መለሰ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እናትአለም መለሰ ከዛሬ ጀምሮ የምታስተናግዳቸው ዓለም አቀፍ፣ አሕጉር አቀፍ እንዲሁም አገር አቀፍ ልዩ ልዩ መድረኮች ከተማችን ለሕጻናት ሁለንተናዊ አስተዳደግ የሚመጥኑ መሠረተ ልማቶችን እውን ለማድረግ በትኩረት እየሰራች መሆኗን ለማሳወቅ ያለመ መሆኑን በትናትነው ዕለት በሰጡት ጋዜጣዊ በመግለጫ ገልፀዋል።
እንደ ቢሮ ኃላፊዋ ገለፃ ከመስከረም 24 እስከ 25 የአፍሪካ ከንቲባዎች የሊደርሺፕ ኢኒሼቲቭ መድረክ፤ ከመስከረም 28 እስከ 29 የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም የልህቀት ማዕከልን ለማቋቋም የሚረዳ ዓለም አቀፍ የምክክር መድረክ እንዲሁም ከመስከረም 28 እስከ ጥቅምት 1/2016 ዓ.ም የሀገር አቀፍ መሪዎች የልምድ ልውውጥ መድረኮችን የምታስተናግድ ሲሆን፣ ለሕጻናት ሁለንተናዊ አስተዳደግ ቀዳሚ ትኩረት በሚሰጥ መልኩ መዲናችን አዲስ አበባ ሦስት ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ትልልቅ መድረኮች ለማከናውን አስፈለጊ ቅድመ ዝግጅት አጠናቃለች ብለዋል።
የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ከጅምሩ አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ የቻልንበት ነው ያሉት የቢሮ ኃላፊዋ በጭር ጊዜ ውስጥ ያስመዘገብናቸው ውጤቶች ስኬታማነት ሀገራዊ እና አህጉራዊ ተሞኩሮ ለመሆን መቻሉን ጨምሮ ተመራጭ እና ብዙዎች ሊማሩበት የሚያስችል በየደረጃው የሚገለጽ ዝርዝር ውጤቶችን የያዘ መሆኑን አስመልክቶ ለሌሎች ልምድ ለማካፈል በመሻት መድረኮቹ የተዘጋጁ መሆኑን አስታውቀዋል ።
እስካሁን ባለው በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕርግራም 2500 የወላጆች እና አሳዳጊዎች የምክር አገልግሎት ሰራተኞች፤ ከ56 በላይ ጤና ጣቢያዎች የቀዳማይ ልጅነት ተኮር የህጻናት እና ወላጆች ጤና ክብካቤ አግልገሎትን መስጠት፤ 6 የፌዴራል ሆስፒታል ባለሙያዎች በሕጻናትና እናቶች ላይ ብቻ ማዕከል አድርገው እንዲሰሩ የሚያስችል ስልጠና ወስደው አገልግሎት መጀመራቸውን ጨምሮ ከተማ አስተዳደሩ 9500 ለሚሆኑ ህጻናት እና ወላጆች በከተማዋ አልሚ ምግብ በማቅረብ ላይ እንደሚገኝ ይፋ አድርገዋል።
ከዚህ በተጨማሪም 46 የቅድመ አንደኛ ደረጃ ት/ቤቶች ወደ ጨዋታ መር የማስተማር ዘዴ እንዲሸጋገሩ ማስቻል፣ በከተማችን ከ 150 በላይ የመጫዎቻን ማልማት ጨምሮ በአሁኑ ወቅት በቀዳማይ ልጅነት ልማት እሳቤዎች የተቃኙ 9 አዳዲስ የመጫዎች ቦታዎችም በተለያዩ አካባቢዎች ለምተው በቅርቡ አገልግሎት በመስጠት እንደሚጀምሩ ገልፀዋል።
በመግለጫቸው ማጠቃለያ ወቅት ኃላፊዋ በሦስቱም መድረኮች ከለውጡ ማግስት አንስቶ በሁሉም ረገድ የጀመርናቸው ሰው ተኮር የልማት ፕሮገራሞች እውቅና እንዲያገኙ ከማስቻል ባለፈ ተሞክሮውን እንደ ሀገር እና አህጉር በማስፋት አህጉራዊ ተቀባይነትና ምሳሌነታችንን በተጨባጭ ለማጉላት የላቀ አስተዋጽኦ የሚኖረው ሲሉ በአንክሮ ተናግረዋል።
ዘገባው የአዲስ አበባ ከተማ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ነው ።