ለትራፊክ ፍሰት መሳለጥ አስተዋፅኦ ያላቸው የአቋራጭ መንገዶች ግንባታ በመከናወን ላይ ነው
አዲስ አበባ፡- መስከረም 18 ቀን 2016 ፣- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በራስ ኃይል በርካታ መጋቢና አቋራጭ መንገዶችን በመገንባት በመዲናችን ዋና ዋና መንገዶች ላይ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጭናነቅ ለመቀነስ እየሰራ ይገኛል፡፡
ባለስልጣኑ በከተማዋ የተለያዩ አከባቢዎች እየገነባቸው ከሚገኙ አቋራጭ መንገዶች መካከል፣ ከፍል ውሃ – ሸራተን ሆቴል፣ ከካሳንችስ – ልማት ባንክ እና ከቤተል ሚካኤል- አንፎ ሜዳ አስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጄክቶች ይጠቀሳሉ፡፡
ከፍልውሃ – ሸራተን የሚወስደው የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት 450 ሜትር ርዝመት በ40 ሜትር የጎን ስፋት እየተገነባ ያለ ነው፡፡
ይህ ፕሮጀክት ከዚህ በፊት ምንም አይነት የመንገድ መስመር ባልነበረው ስፍራ እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን፣ በዋናነት ከታላቁ ቤተ መንግስት ወደ ታችኛው ቤተ መንግስት የሚያደርስ አቋራጭ መንገድ ነው፡፡
ፕሮጀክቱ አሁን ላይ የአፈር ቆረጣ፣ የቱቦ ቀበራ እና ተያያዥ የግንባታ ስራዎች እየተከናወኑለት ይገኛል፡፡
የከተማዋን የመንገድ መረብ ይበልጥ ለማስተሳሰር በራስ ኃይል እየተገነቡ ከሚገኙ አቋራጭ መንገድ ፕሮጀክቶች መካከል ሌላኛው ከካሳንችስ- ልማት ባንክ የሚወስደው መንገድ ነው።
ይህ የአስፋልት መንገድ ፕሮጀክት አጠቃላይ ርዝመቱ 585 ሜትር ሲሆን በ10 ሜትር የጎን ስፋት እየተገነባ የሚገኝ ነው፡፡
ግንባታው አሁን ላይ ከአጠቃላይ የፕሮጀክቱ ርዝመት 300 ሜትር በሚሆነው የመንገድ ክፍል የሰብ ቤዝ ስራው የተጠናቀቀ ሲሆን፣ በቀሪው የመንገዱ ክፍል የውሃ ማስተላለፍያ የኮንክሪት ግንባታ እና ተያያዥ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡
በሌላም በኩል ከቤቴል ሚካኤል ወደ አንፎ ሜዳ አቅጣጫ እየተገነባ የሚገኘው አቋራጭ የልማትአስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀክት 520 ሜትር ርዝመትና በ20 ሜትር የጎን ስፋት እየተገነባ ያለ ነው፡፡
ይህ ፕሮጀክት ከዚህ በፊት በቂ መንገድ ባልነበረው ሥፍራ እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን፣ አሁን ላይ የአፈር ቆረጣ እና የቱቦ ቀበራ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡
ባለሥልጣኑ እነዚህንና ሌሎች አቋራጭ የመንገድ የግንባታ ፕሮጀክቶችን ሙሉ በሙሉ አጠናቆ ለትራፊክ ክፍት በሚደረግበት ወቅት፣ በየአካባቢው የተሻለ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር ከማስቻሉም በላይ፣ የህብረተሰቡን የመግቢያና መውጫ የመንገድ ችግር የሚፈታ ይሆናል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity
ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/
