የሠላምና የፍቅር መገለጫ የሆኑት የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት ትውፊታቸው ተጠብቆ በሠላም በሚከበሩበት ሁኔታ ላይ ያተኮረ የሰራተኞች ውይይት ተካሄደ ።
መስከረም 08 ቀን 2016 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ፤ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን አመራርና ሰራተኞች የ2016 ዓ.ም የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላት ወግና ተውፊታቸው ተጠብቆ፣ በሠላም እንዲከበሩ ለማስቻል በቀረበው ሰነድ ላይ ውይይት አካሂደዋል።
ለውይይት መነሻ የተዘጋጀውን ሰነድ ያቀረቡት የባለሥልጣኑ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ኢያሱ ሰሎምን እንደገለፁት፤ በተባበሩት መንግሥታት የሳይንስ፣ የትምህርትና የባህል ድርጅት በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገቡት ሁለቱም በዓላት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ህዝብ ወደ አደባባይ ወጥቶ የሚያከብራቸው እና በርካታ የውጭ ሀገራት ቱሪስቶችም የሚታደሙባቸው በመሆኑ፣ በዓላቱ ለእምነትና ሥርዓቱ ተከታዮች ካላቸው የተለየ ፋይዳ ባሻገር፣ የሀገራችንን መልካም ገፅታ በመገንባት እና የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትም ጭምር አስተዋፅኦ እንዳላቸው ጠቁመዋል።
በዓላቱ በሠላም እንዲከበሩ ለማስቻል በቂና የተቀናጀ ዝግጅት መድረጉን የጠቆሙት የባለሥልጣኑ የሬጉላቶሪ ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ታከለ ሉሌና በበኩላቸው ሁላችንም ለሠላም ቅድሚያ በመስጠት በዓላቱ በድምቀት እንዲከበሩ አስፈላጊውን ድጋፍና ትብብር ከማድረግ ጎን ለጎን፣ አጠራጣሪ ሁኔታዎች ሲያጋጥሙ ለፀጥታ አካላት መረጃ በመስጠት በዓላቱ ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲከበሩ የበኩላችንን ሚና መወጣት ይጠበቅብናል ብለዋል።
የባለሥልጣኑ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር አብነት ዳምጣቸውእንደገለፁት በዓላቱ ኢትዮጰያዊያንን በዓለም አደባባይ ያስተዋወቁ መሆናቸውን ጠቅሰው፣ በዓላቱ በአደባባይ የሚከበሩ በመሆናቸው፣ በመደበኛነት ከሚከናወኑ ልዩ ልዩ የመንገድ ጥገና ሥራዎች በተለየ ለበዓላቱ ድምቀት መጠነ ሰፊ የመንገድ ጥገና ሥራዎች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው፣ ይሄው ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልጸዋል።
በውይይቱ የተሳተፋት የባለሥልጣኑ የሥራ መሪዎች በበኩላቸው ሁለቱም በዓላት የአደባባይ በዓላት በመሆናቸው ዓለም አቀፍ ትኩረት የሚስቡ፣ ብዙ ቱሪስቶች የሚገኙባቸው እና ለሀገር ገፅታ ግንባታ ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸው በመሆኑ በዓላቱ በሠላምና በድምቀት እንዲከበሩ የበኩላችንን ድርሻ እንወጣለን ብለዋል ።
በተመሳሳይም በተቋሙ ሁሉም የሥራ ክፍሎች በሰነዱ ላይ ውይይት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity