በመንገድ ግንባታ ሂደት የኮንትራት ውል አስተዳደር ላይ ያተኮረ የአቅም ግንባታ ስልጠና ተሰጠ
ነሀሴ 23 ቀን 2015 ዓ.ም፣ አዲስ አበባ – የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በመንገድ ግንባታ ሂደት ላይ የኮንትራት ውል ስርአት አተገባበር ላይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል የአቅም ግንባታ ስልጠና ለባለሙያዎች ተሰጠ፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክት ማኔጅመንት ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር በተሰጠው ስልጠና ላይ የመንገድ ግንባታና ጥገና፣ ጥራት ማረጋገጥ፣ የኮንትራት አስተዳደር እና ዲዛይን ፣ የህግ ባለሙያዎች እንዲሁም ከስራው ጋር ተዛማጅ የሆኑ ባለሙያናዎች ስልጠናውን ወስደዋል፡፡
ስልጠናውን የሰጡት የምህንዲስና ውል ጉዳዮች ባለሙያ ኢንጂነር ዮሴፍ ኪዳኔ ስልጠናው በኮንስትራክሽን ስራዎች ዙሪያ ያሉ የህግ አግባቦች እና የኮንስትራክሽን ውል ስርአት ሂደት ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን እንዴት መፍታት እንደሚቻል ግንዛቤ የሚሰጥ ነው ብለዋል፡፡
ኢንጂነር ዮሴፍ አክለውም በስልጠናው የኮንስትራክሽን የግንባታ ውለታ አስተዳዳር ሂደት ላይ የመንገድ ግንባታው ተገንብቶ እስከሚጠናቀቅ ድረስ የሚታዩ ችግሮችን ላይ ትኩረት ያደረገና በተለይም በስራ ተቋራጭ እና ባለቤት መካከል የሚኖሩ አለመግባባቶችን እንዴት መፍታት ይቻላል የሚል መሠረታዊ ግንዛቤዎችን የሚያስጨብጥ ነው ብለዋል፡፡
በመጨረሻም እንዲህ አይነት ስልጠናዎች በየጊዜው ለባለሙያዎች መሰጠቱ በአሰሪ ተቋማትና በስራ ተቋራጮች መካከል በግንባታ ሂደት የሚከሰቱ አለመግባባቶች እና የሀብት ብክነት እንዳይኖር ለመከላከል የሚረዱ በመሆናቸው ባለሙያዎቹ ተገቢውን የህግ አግባብና የኮንትራት አካሄድ እንዲያውቁ ከማድረግም ባለፈ በስራቸው ላይም እንዲተገብሩት መደረጉ ጥቅሙ ዘርፈ ብዙ ነው ብለዋል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በቀጣይም የባለሙያዎችን የስራ አቅም ሊያዳብሩ የሚችሉ አስራ ሁለት አይነት ልዩ ልዩ ሙያዊ ስልጠናዎችን የሚሰጥ ይሆናል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity