የሚዲያ ባለሙያዎች በከተማዋ በግንባታ ላይ የሚገኙ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ
አዲስ አበባ፣ነሀሴ 25 ቀን 2015 ዓ.ም፡- ከተለያዩ የግልና የመንግስት የሚዲያ ተቋማት የተውጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በከተማዋ በግንባታ ላይ የሚገኙ ግዙፍ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በዛሬው ዕለት ጎብኝተዋል፡፡
በመንገድ ጉብኝቱ ላይ ተገኝተው ለሚዲያ ባለሙያዎቹ ገለፃ ያደረጉት የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የለህብረተሰቡ የመንገድ መሠረተ-ልማት ጥያቄ የሚመልሱ እና የከተማዋን ገፅታ እየቀየሩ ያሉ በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች እየተገነቡ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡
ኢንጂነር ሞገስ አክለውም በከተማዋ የሚስተዋለውን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ለመፍታት ከ2.7 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ 6 የትራፊክ ማሳለጫ ተሸጋጋሪ ድልድዮች በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች እየተገነቡ መሆናቸውን ለጉብኝቱ ተሣታፊዎች ገልፀዋል፡፡
ባለፉት 5 ዓመታት 82 የሚሆኑ የመንገድ ፕሮጀክቶች ግንባታቸው ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት መደረጋቸውን ያወሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ በቀጣይም የከተማዋ የትራፊክ ፍሰት የሚያሳልጡና ገፅታዋን የሚቀየይሩ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት በዕቅድ መያዙን አስታውቀዋል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ አስተባባሪነት የተዘጋጀው ይህ የሚዲያ ባለሙያዎች ጉብኝት ፕሮግራም በከተማዋ በግንባታ ላይ ስለሚገኙ የልማት ፕሮጀክቶች በቂ ግንዛቤ እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው የጉብኝቱ ተሣታፊዎች ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity