+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የቤት ዕድሳት መርሃ ግብር ተጀመረ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 19 ቀን 2015 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በዛሬው ዕለት በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 11 በተለምዶ 30 ቀበሌ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የአቅመ ደካሞች ቤት እድሳት ስራ በይፋ አስጀምሯል፡፡

በቤት እድሳት ማስጀመሪያ ስነስርዓት ላይ የተገኙት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በዘንድሮው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር አብረውት ከሚሰሩ አጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር 20 የሚሆኑ የአቅመ ደካማ ነዋሪዎችን የመኖሪያ ቤት እድሳት በቀጣይ ሁለት ወራት ውስጥ አጠናቆ ለማስረከብ ዕቅድ መያዙን ገልፀዋል፡፡

ኢንጂነር ሞገስ አያይዘውም ባለስልጣኑ ከሚሰራቸው መደበኛ የግንባታና የጥገና ስራዎች በተጨማሪ በርካታ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎችን እንደሚያከናውን ጠቅሰው፣ ባለፉት 4 ዓመታት ውስጥ የ24 አቅመ ደካሞች ቤት እድሳት ስራ አጠናቆ ለተጠቃሚዎች ማስረከቡን ገልፀዋል።

የባለሥልጣኑ ሠራተኞች በ2015 ዓ.ም የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት መርሃ ግብር በህፃናት ድጋፍ፣ በችግኝ ተከላ፣ በደም ልገሳ እና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ምድረ ግቢ እድሳት ስራዎች እየተሳተፉ እንደሚገኙ ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የሚያካሂደው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራ ውጤታማ እንዲሆን ድጋፍ እያደረጉ ለሚገኙ አጋር ድርጅቶች ምስጋናቸውን ያቀረቡት ዋና ዳይሬክተሩ ሌሎች ባለድርሻ አካላትም ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ በበጎ አድራጎት ስራዎች ላይ ተሳትፏቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.