በከተማዋ የድሬኔጅ መስመር ፅዳትና ጥገና ሥራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 17 ቀን 2015 ዓ.ም ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በክረምት ወቅት የሚያጋጥመውን የጎርፍ አደጋ ስጋት ለመከላከል ከሚያከናውናቸው የተለያዩ የግንባታና ጥገና ሥራዎች ጎን ለጎን በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የመንገድ ዳር የዝናብ ውሃ መፋሰሻ መስመሮችን በማፅዳትና በመጠገን ላይ ይገኛል፡፡
የነሐሴ ወር የአየር ትንበያ መረጃ እንደሚያመለክተው አንድንድ የሀገሪቱ ክፍሎች መደበኛና ከመደበኛ በላይ የዝናብ መጠን እንደሚያገኙ የሚጠበቅ ከመሆኑም በተጨማሪም በፀሐይ ኃይል ታግዘው ከሚፈጠሩ የደመና ክምችቶች በረዶ የቀላቀለ ቅፅበታዊ ጎርፍ ሊያስከትል የሚችል ከባድ ዝናብ ሊከሰት እንደሚችል ይገመታል፡፡
በመሆኑም የክረምቱን የአየር ሁኔታ ታሳቢ በማድረግ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚካሄደው የድሬኔጅ መስመር ፅዳትና ጥገና ሥራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው፡፡
ባሳለፍነው ሳምንት የድሬኔጅ መስመር ጥገና ከተደረገላቸው አከባቢዎች መካከል ኮልፌ ክፍለ ከተማ ጎመን ሰፈር፣ አማኑኤል ቤተ ክርስትያን ፊት ለፊት፣ ከአራት ኪሎ -ፒያሳ፣ ከቦሌ አደባባይ – መስቀል አደባባይ፣ መርካቶ ሸራ ተራ አካባቢ፣ አስኮ ኮንዶሚንየም፣ ከጣፎ አደባባይ – አያት፣ ከሲ.ኤም.ሲ አደባባይ – አቤም ሆቴል፣ ከሲ.ኤም. ሲ ሚካኤል – መገናኛ፣ ሻራተን ሆቴል፣ ከኢምፔሪያል አደባባይ – ሮባ ዳቦ፣ ከአትላስ – ሩዋንዳ፣ ኃይሌ ጋርመንት፣ ከጀርመን አደባባይ – መካኒሳ እና ማንጎ ጨፌ ሃዩንዳይ ሞተርስ ጀርባ አከባቢ ይጠቀሳሉ፡፡
በከተማዋ የመንገድ ዳር ውሃ መፋሰሻ መስመሮችና በሌሎች የመንገድ አካላት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ህገወጥ ድርጊቶችን በመከላከል በኩል ባለድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ባለስልጣኑ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity