ቦሌ ኤርፖርት – ጎሮ የመንገድ ፕሮጀክት፣ ሌላው የከተማዋ ውበት፤
አዲስ አበባን ለኑሮና ለሥራ ምቹ የሆነች ዘመናዊ ከተማ ለማድረግ እየተሰሩ ከሚገኙ የተለያዩ የከተማ ልማት ሥራዎች አንዱ የመንገድ ዘርፍ ሥራ ነው፡፡
የከተማዋ የመንገድ መረብ ይበልጥ እንዲተሳሰር፣ ቀልጣፋና ምቹ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር እና ለሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ተደራሽ የሆነ የመንገድ መሰረተ ልማት እንዲኖር በተለያዩ የከተማዋ ማዕዘናት አዳዲስ እና የነባር መንገዶች ማሻሻያ ግንባታ በመከናወን ላይ ይገኛል፡፡
የከተማዋን ገፅታ ትርጉም ባለው መልኩ እየቀየሩና ዘመናዊ የከተማ ገፅታ እያላበሱ ከሚገኙ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል የቦሌ ኤርፖርት – ጎሮ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ይገኝበታል፡፡
ይህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ከቦሌ ብራስ የቀለበት መንገድ መጋጠሚያ ተነስቶ በቦሌ ኤርፖርት በኩል ወደ ጎሮ ቀለበት መንገድ የሚደርስ ሲሆን፣ በአጠቃላይ 4.9 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 60 ሜትር የጎን ስፋት ያለው አዲስ የመንገድ ፕሮጀክት ነው፡፡
የመንገድ ፕሮጀክቱ ከቱሉ ድምቱ የክፍያ መንገድ አቅጣጫ በጎሮ በኩል ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ ተሽከርካሪዎች የትራፊክ መጨናነቅ ሳይገጥማቸው በቀጥታ ወደ መሀል ከተማ ለመግባት በአማራጭነት ሊጠቀሙበት የሚያስችል ምቹ እና አቋራጭ መንገድ ነው፡፡
የመንገድ ፕሮጄክቱ ሰፊና ምቹ የተሸከርካሪ መተላለፊያ መስመር፣ ማራኪና በቂ የእፅዋት ሥፍራን አካቶ እየተገነባ የሚገኝ ከመሆኑም በተጨማሪ ለሁሉም የህበረተሰብ ክፍል ተደራሽ የሆነ የእግረኛ መንገድ እና የሞተር አልባ ትራንስፖርት እንቅስቃሴን የሚያበረታታ ምች የፔዳል ሳይክል መተላለፊያ መንገድ አለው፡፡
በዚህ ደረጃ እየተገነባ የሚገኘው ይህ ዘመናዊ መንገድ ከቦሌ ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያ ጋር የተሳሰረ በመሆኑ የከተማዋ ኢኮኖሚያሚና ማህበራዊ እድገት እንዲፋጠን ከሚያበረክተው ጉልህ አስተዋፅኦ ባሻገር ለከተማዋ ተጨማሪ ውበት እንደሚያላብስ ይታመናል፡፡
የግንባታ ስራው ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አሰር ኮንስትራክሽን በተባለ ሀገር በቀል የስራ ተቋራጭ እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን የማማከርና የክትትል ስራውን ደግሞ ዩኒኮን አማካሪ ድርጅት እያከናወነው ይገኛል፡፡
ፕሮጀክቱ አሁን ላይ ከቦሌ ብራስ የቀለበት መንገድ መጋጠሚያ ጀምሮ ወደ ቦሌ ጉምሩክ አቅጣጫ 1.3 ኪሎ ሜትር የሚሆነው የመንገዱ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ አስፋልት ለብሶ አገልግሎት እየሰጠ ይገኛል፡፡
ከጉምሩክ ጀምሮ እስከ መጨረሻ ያለው ቀሪው የመንገዱ ክፍል ላይ ደግሞ የሙሌት፣ የድሬኔጅ መስመር ዝርጋታ፣ የድልድይ፣ የከልቨርት ቦክስና የድጋፍ ግንብ ስራ በመከናወን ላይ ነው፡፡ አጠቃላይ አፈፃፀሙም 47.1 በመቶ ደርሷል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity