ባለስልጣን መሰሪያ ቤቱ ለሚደግፋቸው 50 ሕፃናት ከ223ሺብር በላይ ግምት ያለው የኑሮ ድጎማ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ነሀሴ 1 ቀን 2015ዓ.ም፣- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን በየዓመቱ ከሚያደርገው የክረምት የበጎ ፍቃድ ተግባራት መካከል የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ሰራተኞች በቋሚነት ለሚደግፏቸው 50 ህፃናት 223 ሺ250 ብር ግምት ያላቸው የምግብ ቁሳቁሶች ድጋፍ አድርጓል፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በየወሩ ከሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ አሁን ላይ ያለውን የኑሮ ጫና በመረዳት ለ50 ህፃናት ለእያንዳንዳቸው 4 ሺህ 465 ብር ግምት ያላቸው 35 ኪሎ ግራም የስንዴ ዱቄትና 10 ሊትር የምግብ ዘይት ድጋፍ ተሰጥቷል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን የተቋም አቅም ግንባታ ሲስተም ዲዛይን ዳይሬክተር ወ/ሮ አበዜ ሱሌይማን እንደገለፁት፣ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የህብረተሰቡን የኑሮ ጫና ለማቃለል በቋሚነት 50 ለሚሆኑ ህፃናት በየወሩ ከሚያደርገው የገንዘብ ድጋፍ በተጨማሪ የማዕድ ማጋራት እና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ችግሮችን በማቃለል በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እየተወጣ የሚገኝ ተቋም መሆኑን ጠቁመው፣ በመጪው አዲስ ዓመትም የበዓል ስጦታ ድጋፍ ለማድረግ እቅድ ይዞ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
በጳጉሜ ወር 2014 ዓ.ም ለ50 ህፃናት ለእያንዳንዳቸው 3800 ብር እና የተለያዩ የምግብና የንፅህና መጠበቂያ ቁሳቁሶች የአዲስ ዓመት ስጦታ ድጋፍ መደረጉ ይታወሳል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ:-
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity