የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ አመራርና ሠራተኞች 25 ሺህ የአፕል ችግኞችን በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አሳርፈዋል
አዲስ አበባ፣ ሀምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አመራርና ሠራተኞች የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ጠቅላይ ሚኒስተር ዶ/ር አብይ አህመድ በተገኙበት 25 ሺህ የአፕል ችግኞችን በመትከል የታሪካዊው ሀገር አቀፍ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካል ሆነዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ እንደገለፁት፤ ለሰው ልጆች ጤና ከፍተኛ ጥቅም ያላቸው የአፕል ችግኞችን መትከል መቻላችን የከተማችንን አረንጓዴ ሽፋን እጥፍ ድርብ ጠቀሜታ ባላቸው የእፅዋት ዝርያዎች ለማልበስ የሚያግዝ እና የከተማ ግብርናን በፍራፍሬ ልማት የማሳደግ አሰራርን የሚያጎለብት ነው ብለዋል፡፡
ባለስልጣን መ ስሪያ ቤቱ በተያዘው የክረምት ወቅት የዛሬውን ጨምሮ አጠቃላይ 50 ሺ ችግኞችን ለመትከል ማቀዱን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሩ፤የተተከሉ ችግኞችም መፅደቃቸው እስከሚረጋገጥ ድረስ በየጊዜው የመንከባከቡ ስራ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ኢያሱ ሰሎሞን በበኩላቸው የአረንጓዴ እፅዋት ሽፋንን ማሳደግ ምቹ የአየር ሁኔታ እንዲፈጠር የሚያግዙ እና ከምግብነት ባለፈ ለጤና በረከት የሚሰጡ የአፕል ችግኞችን መትከል መቻላችን የዘንድሮውን የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር የተለየ እንደሚያደርገው ግልፀዋል፡፡
አቶ ኢያሱ አያይዘውም ችግኞቹ የተተከሉበት ቦታ ከሰውና ከእንስሳት ንክኪ ነፃ ከመሆኑም በላይ በኮምፖስት ማዳበሪያ የታገዘ በመሆኑ የመፅደቅ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በችግኝ መርሀ ግብሩ ላይ የተሳተፉት ሌሎች አመራርና ሠራተኞችም “ነገን ዛሬ እንትከል’ በሚል መሪ ሀሳብ በተካሄደው ሀገር አቀፍ መርሃ ግብር ላይ መሳተፋቸው እንዳስደሰታቸው አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity