+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

የከተማዋ አማራጭ የመውጫና መግቢያ ኮሪደር መንገድ ግንባታ

ከደቡባዊ አዲስ አበባ ቃሊቲ አደባባይ ተነስቶ በደቡባዊ ምስራቅ አቅጣጫ የሚገኙትን ቡልቡላ እና አቃቂ ወንዞችን ተሻግሮ ቂሊንጦ ሁለተኛ ቀለበት መንገድ አደባባይ ላይ የሚገናኘው የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ 85 በመቶ የፊዚካል አፈፃፀም ላይ ደርሷል፡፡

ይህ የመንገድ ፕሮጀክት ግንባታ ሙሉ ለሙሉ ሲጠናቀቅ ከቃሊቲ አደባባይ እስከ ቱሉ ዲምቱ አደባባይ ካለው ግዙፍ የመንገድ ፕሮጀክት በተጨማሪ የከተማዋ አማራጭ የመግቢያና መውጫ ኮሪደር በመሆኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎችን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳለጥ ሩብ ጉዳይ ቀርቶታል፡፡

ይህ የመንገድ ፕሮጀክት በበጀት እጥረትና በወሰን ማስከበር ችግሮች ምክንያት ለተወሰነ ጊዜ የግንባታ ሂደቱ የተጓተተ ቢሆንም በተያዘው በጀት ዓመት ችግሩ ተፈትቶ የግንባታ ስራው ዳግም መጀመሩ የሚታወስ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት የመንገድ ፕሮጀክቱ አንድ አካል የሆነውና 325 ሜትር ርዝመት ያለው የማሳለጫ ድልድይ ግንባታ 75 በመቶ ተጠናቆ በስተግራ በኩል ያለው መስመር ለትራፊክ ክፍት ተደርጓል፡፡

ባለስልጣኑ የድልድዩን እና ቀሪ የመንገድ ፕሮጀክቱን የግንባታ ስራዎችንም በአጭር ጊዜ ውስጥ አገባዶ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ እየሰራ ይገኛል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ ካለው አጠቃላይ 10.5 ኪ.ሜ ርዝመት ውስጥ 5.6 ኪ.ሜ የሚሆነው የአስፋልት ንጣፍ የተከናወነለት ሲሆን ቀሪው የመንገዱ ክፍል ላይ ደግሞ የአፈር ቆረጣ ስራው ተጠናቆ የገረጋንቲ አፈር ሙሌት ስራዎች በመከናወን ላይ ይገኛሉ፡፡

ይሁን እንጂ ከፕሮጀክቱ መነሻ 150 ሜትር ርዝመት ላይ ከፍተኛ የውሀ መስመር፣የቴሌ ፋይቨሮች እና የኮንክሪት ፖሎች እስካሁን ድረስም ሙሉ ለሙሉ መነሳት ባለመቻላቸው የግንባታ ስራውን በሚፈለገው መጠን ማከናዎን አልተቻለም፡፡

የግንባታ ስራውን ቻይና ኮንስትራክሽን ኮሚኒኬሽን ካምፓኒ ከ2.3 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ እያከናወነው ሲሆን የማማከርና የቁጥጥር ስራውን ደግሞ ሀይ ዌይ ኢንጂነርስ አማካሪ ድርጅት እና ኤም ቲ ኤስ ኢንጂነሪንግ በጋራ በመሆን እየተከታተሉት ይገኛሉ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.