+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

የዝናብ ውሃ መፋሰሻ መስመሮች ጥገና እና መልሶ ግንባታ ስራ ተጠናክሮ እንደቀጠለ ነው

ሰኔ 11 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን የመንገድ ዳር የዝናብ ውሃ መፋሰሻ መስመሮችን ደህንነት በመፈተሽ የፅዳት፣ የጥገና እና የመልሶ ግንባታ ስራ በስፋት እያከናወነ ይገኛል፡፡

በከተማዋ ጎዳናዎች የእግረኛ መተላለፊያ መንገዶች ስር የተዘረጉት የዝናብ ውሃ መፋሰሻ መስመሮች በአጠቃቀም ጉድለት ሳቢያ በተደጋጋሚ ብልሽት ይገጥማቸዋል፡፡

የዝናብ ውሃ መፋሰሻ መስመሮች ብልሽት አመላካች ከሆኑ ችግሮች መካከል የድሬኔጅ መስመሩ በደረቅ ቆሻሻዎች መደፈን፣ በደለል መሞላት እና በተለያየ ምክንያት የመፍረስ አደጋ የሚገጥማቸው መሆኑ ይጠቀሳል፡፡

ባለስልጣን መሰሪያ ቤቱ ባለፉት 11 ወራት ባከናወነው የድሬኔጅ መስመር ክትትልና ጥገና ሥራ ከ370 ኪሎ ሜትር በላይ ርቀት የሚሸፍን የዝናብ ውሃ መፋሰሻ መስመሮች ፅዳትና ጥገና አከናውኗል፡፡

የክረምቱን ወቅት መግባት ተከትሎ የዝናብ ውሃ መፋሰሻ መስመሮች ፅዳትና ጥገና ሥራው ተጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፣ ባሳለፍነው ሳምንት የጐርፍ አደጋ ስጋት አለባቸው ተብለው በተለዩት በአማኑኤል ሆስፒታል አካባቢ፣ በሠፈረ ሠላም፣ በጥይት ቤት፣ በመንዲዳ እና በሲ.ኤም.ሲ አካባቢዎች የድሬኔጅ መስመሮች ጥገና ስራ ተከናውኗል፡፡

በክረምቱ ወቅት ሊከሰት የሚችለውን የጎርፍ አደጋ ስጋት ከወዲሁ ለመከላከል ሕብረተሰቡ ቆሻሻዎችን ወደ መንገድ ጋር የውሃ መፋሰሻ መስመሮች ባለመጣል እና በየአካባቢው የሚገኙ ክፍት የውሃ ማስተላለፊያ መስመሮችን በማፅዳት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ መልእክቱን ያስተላልፋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.