+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

የከተማዋ ዓይነ ግቡ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ ከተማ እየተገነቡ የሚገኙ አዳዲስ መንገዶች በዲዛይን ይዘታቸውም ሆነ በግንባታ የጥራት ደረጃቸው የላቁ በመሆናቸው፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣት ላይ የሚገኘውን የከተማዋን የትራፊክ እንቅስቃሴ በተሻለ ሁኔታ የማስተናገድ አቅም ያላቸው ከመሆኑም ባሻገር ለከተማዋም ተጨማሪ ውበት የሚያጎናፀፉ ናቸው፡፡

አሁን ላይ በግንባታ የማጠናቀቂያ ምዕራፍ ላይ ከሚገኙ የመንገድ ግንባታ ፕሮጄክቶች መካከል አንዱ የሆነው እና 300 ሜትር ርዝመት ያለው የትራፊክ ማሳለጫ ድልድይ የተገነባበት የኤምፔሪያል የመንገድ መጋጠሚያ ማሻሻያ ፕሮጄክት ይህንኑ እውነታ ከሚያረጋግጡ የመንገድ ትሩፋቶች አንዱ ነው፡፡

ቀደም ሲል በኤምፔሪያ አደባባይ ላይ ይከሰት የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ለመፍታት አደባባዩን የማንሳትና በትራፊክ መብራት የመተካት መፍትሄ ተሰጥቶ የነበረ ቢሆንም፣ ቀለበት መንገዱና የአካባቢው መቃረቢያ መንገዶች የሚያስተናግዱት የትራፊክ ፍሰት እየጨመረ በመምጣቱ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የኤምፔሪያል የትራፊክ ማሳለጫ ድልድይ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡

ይህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በቻይና ፈርስት ሃይ ዌይ ኢንጂነሪንግ እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን የማማከርና የቁጥጥር ስራው በስታዲያ ኢንጂነሪንግ ስራዎች አማካሪ ድርጅት በኩል እየተሰራ ይገኛል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ ከማሳለጫ ድልድዩ በተጨማሪ የመቃረቢያ መንገዶቹን ጨምሮ በአጠቃላይ 1.8 ኪሎ ሜትር ርዝመትና 40 ሜትር የጎን ስፋት አለው፡፡ ለፕሮጄክቱ ማስፈፀሚያም ከ714.8 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት በከተማ አስተዳደሩ ተመድቦለታል፡፡

በአሁኑ ወቅት የማሳለጫ ድልድዩ ግንባታ በከፊል ተጠናቆ በሁለቱም አቅጣጫ ለትራፊክ ክፍት የተደረገ ሲሆን፣ አጠቃላይ የፊዚካል አፈፃፀሙም 77.4 በመቶ ላይ መድረስ ችሏል፡፡ ቀሪውን የግንባታ ስራም በአጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.