ከቃሊቲ ቶታል- አቃቂ ድልድይ- ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀከት አስፋልት የመንጠፍ ስራ እየተከናወነ ነው
ሰኔ 7 ቀን 2015 ዓ.ም አዲስ አበባ፡- ከቃሊቲ ቶታል – አቃቂ ድልድይ – ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ግንባታ ኘሮጀክት የመጨረሻ ደረጃ አስፋልት የማንጠፍ ስራ በመከናወን ላይ ነው፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በራስ ኃይል ከሚገነባቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ በሆነው የቃሊቲ ቶታል- አቃቂ ድልድይ- ቱሉ ዲምቱ የአስፋልት መንገድ ግንባታ ፕሮጀከት ላይ ቀሪ የወሰን ማስከበር ስራ በወቅቱ ባለመጠናቀቁ የግንባታ ስራው ከታሰበለት ጊዜ በላይ የተራዘመ ቢሆንም፣ አሁን ላይ የወሰን ማስከበር ችግሮች በመፈታታቸው የግንባታ ስራው እየተፋጠነ ይገኛል፡፡
ቀደም ሲል ተገንብቶ አገልግሎት እየሰጠ የቆየው ነባር መንገድ ከሰባት ሜትር ያልበለጠ ስፋት የነበረውና ጠባብ ከመሆኑም በተጨማሪ የእግረኛ መንገድ የሌለው በመሆኑ በአካባቢው የነበረውን የትራፊክ እንቅስቃሴ አስቸጋሪ አድርጎት ቆይቷል፡፡
ለረጅም ዓመታት በማገልገሉ ምክንያት በከፍተኛ ደረጃ ተጎድቶ የነበረውን ነባር መንገድ በማንሳት በአዲስ መልክ ተሻሽሎ በመገንባት ላይ የሚገኘው ይህ መንገድ አጠቃላይ ርዝመቱ 5.6 ኪሎ ሜትር ሲሆን፣ የእግረኛ መንገድን ጨምሮ 25 ሜትር የጎን ስፋት አለው፡፡
የመንገድ ግንባታ ስራው ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ሲጀምር በዋናነት የአካባቢውን ነዋሪዎች ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ከማሳደጉም በተጨማሪ ከቃሊቲና ቱሉዲምቱ አካባቢ ለሚመጡ ተሽከርካሪዎች ወደ አቃቂ እና ገላን ለመሄድ በአቋራጭነት የሚያገለግል ይሆናል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity