+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ከቃሊቲ እስከ ቱሉ ዲምቱ በወፍ በረር ቅኝት

በአዲስ አበባ ከተማ በመገንባት ላይ ከሚገኙ ግዙፍ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች መካከል ከቃሊቲ አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ ድረስ የሚዘልቀውና 11 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው የመንገድ ፕሮጀክት ቀዳሚውን ቦታ የሚይዝ ነው፡፡

የቃሊቲ -ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክትን ግዙፍነት አጉልተው ከሚያሳዩ የመንገዱ ገፅታዎች መካከል በመንገድ ፕሮጀክቱ 3 ቦታዎች ላይ የተገነቡት የትራፊክ ማሳለጫ ተሸጋጋሪ ድልድዮች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ በተለያዩ ዋና ዋና የመንገድ መጋጠሚያ ሥፍራዎች ላይ የመንገድ ፕሮጀክቱ አካል ሆነው የተገነቡት እነዚህ የትራፊክ ማሳለጫ ድልድዮች ለመንገድ ፕሮጀክቱ ተጨማሪ ድምቀትን ያጎናፀፉ ናቸው፡፡

የፕሮጀክቱ መነሻ በሆነው የቃሊቲ ማሰልጠኛ ቀለበት መንገድ መጋጠሚያ ላይ ተገንብቶ፣ አሁን ላይ የማጠናቀቂያ ግንባታ ሥራ እየተከናወነበት የሚገኘው የመጀመሪያው ማሳለጫ ድልድይ 240 ሜትር ርዝመት አለው፡፡

የማሳለጫ ድልድዩ የቀድሞውን የቀለበት መንገድ አደባባይ ሳይነካ በቁመት ከፍ ብሎ የተገነባ በመሆኑ የትራፊክ እንቅስቃሴውን ከማሳለጡ ባሻገር ለአካባቢው ገፅታም ልዩ ውበት የሚያላብስ ነው፡፡

በቀለበት መንገዱ ላይ የተገነባው ይህ የማሳለጫ ድልድይ፣ ከሳሪስ አቦ የሚመጣውን ትራፊክ ተቀብሎ ወደ ቃሊቲ የሚያሸጋግር ሲሆን ከስር ያለው ነባሩ አደባባይ ደግሞ ወደ ሳሪስ አቦ እና ወደ ኃይሌ ጋርመንት አደባባይ ለሚተላለፉ ተሽከርካሪዎች ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡

የዚሁ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት አካል የሆነው ሁለተኛው የማሳለጫ ድልድይ ደግሞ፣ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፣ ከሥር ወደ አቃቂ ከተማ ለመግባትና ለመውጣት የሚያገለግል፤ ከላይ ደግሞ በቀጥታ ወደ ቱሉ ድምቱ እና ቃሊቲ አደባባይ በግራና ቀኝ የሚተላለፈውን የትራፊክ ፍሰት በሚገባ የሚያሳልጥ ነው፡፡

ይህ የማሳለጫ ድልድይ 90 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን አሁን ላይ የግንባታ ስራው በመገባደዱ ለትራፊክ አገልግሎት ክፍት ሆኗል፡፡

ሦስተኛውና የመጨረሻው የትራፊክ ማሳለጫ ተሸጋጋሪ ድልድይ ደግሞ፣ ቀደም ሲል ጋሪ ድልድይ እየተባለ በሚጠራው ሥፍራ የተገነባውና 50 ሜትር ርዝመት እና 20 ሜትር የጎን ስፋት እንዲኖረው ተደርጎ በአዲስ መልክ የተገነባው ተሸጋጋሪ ደልድይ ነዉ፡፡

የቃሊቲ አደባባይ- ቱሉ ድምቱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 11 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚሸፍን ሲሆን በ2.4 ቢሊዮን ብር የግንባታ ዋጋ በቻይናው ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ (CCCC) እየተገነባ የሚገኝ ሲሆን, ኢንጂነር ዘውዴ አማካሪ ድርጅት ደግሞ የማማከርና የቁጥጥር ስራውን እየተከታተለው ይገኛል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.