ባለፉት አስር ወራት ከ12 ሺህ በላይ የመንገድ ዳር መብራቶች ተጠግነዋል
አዲስ አበባ፣ ሰኔ 1 ቀን 2015ዓ.ም፣- የከተማዋን ጎዳናዎች ለትራፊክ እንቅስቃሴ ምቹ ለማድረግ በአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን እየተከናወኑ ከሚገኙ የመንገድ መሰረተ-ልማት አቅርቦቶች መካከል የመንገድ ዳር መብራቶችን የማዘመን እና የመጠገን ስራ ይገኝበታል፡፡
ቀደምሲል በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች ተዘርግተው አገልግሎት እየሰጡ የሚገኙ የመንገድ ዳር መብራቶች በየጊዜው በሚፈፀምባቸው ስርቆትና የተሸከርካሪ ግጭት ምክንያት የአገልግሎት መቆራረጥ ችግር እያስከተለ ቢሆንም፣ ባለሥልጣን መስሪያቤቱ የመንገድ ዳር መብራቶችን መልሶ የመጠገን እና የተሻለ የብርሃን ሽፋን ባላቸው ኤል.ኢ.ዲ አምፖሎች የመተካት ሥራ አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡
ባለፉት 10 ወራት ብቻ 12,473 የመንገድ መብራት አምፖሎችን በመቀየርና በተለያየ ምክንያት ጉዳት የደረሰባቸውን ምሰሶዎችን በመጠገን ለአገልግሎት አብቅቷል፡፡
በመዲናችን ጎዳናዎች ላይ የተዘረጉት የመንገድ ዳር መብራቶች ሚፈነጥቁት ብርሃን ለምሽቱ የትራፊክ እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታን ከመፍጠር ባሻገር ለአዲስ አበባ ከተማ ተጨማሪ ውበት እያጎናፀፉ ቢሆንም፣ ከመሬት በታች በተዘረጉ የኤሌክትሪክ መስመር ገመዶችና ልዩ ልዩ የመንገድ መብራት አካላት ላይ በሚፈፀም ተደጋጋሚ ስርቆት ሳቢያ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች የመንገድ መብራት አገልግሎት እንዲቆራረጥ ምክንያት ሆኗል፡፡
በሌላም በኩል በተሽከርካሪ ግጭት ሳቢያ በመንገድ ዳር መብራቶች ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ለአገልግሎቱ መቆራረጥ ምክንያት እየሆኑ ከሚገኙ ምክንያቶች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡
የመንገድ ዳር መብራት ከአደጋ የፀዳ የትራፊክ እንቅስቃሴ እንዲኖር እና የዜጎች ደህንነት በአስተማማኝ መልኩ እንዲጠበቅ ጉልህ ሚና የሚያበረክት በመሆኑ ባለሥልጣኑ ከ69.7 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የመንገድ ዳር መብራትና ሌሎች የድንገተኛና አንስላሪ ሥራዎችን አከናውኗል፡፡
የመንገድ ዳር መብራት የማዘመን እና የመጠገን ስራ በመጪው የክረምት ወራትም ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity
ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/
ድረ ገፃችንን ይጎብኙ :- http://www.aacra.gov.et