+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

በልዩ ልዩ ግንባታ ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ አካላት በመንገድ ሃብት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን እንዲከላከሉ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም፡- በአዲስ አበባ ከተማ በተለያዩ የግንባታ ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ አካላት በመንገድ ሃብት ላይ ጉዳት የሚያደርሱ ህገ-ወጥ ድርጊቶችን በመከላከል በኩል የበኩላቸውን ገንቢ ሚና እንዲወጡ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን አሳሰበ፡፡

በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄዱ ባሉ የግንባታ ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ የሥራ ተቋራጮች እና ባለንብረቶች የግንባታ ግብዓቶችና ተረፈ ምርቶችን በማጓጓዝና በማከማቸት ሂደት በመንገድ ሀብት ላይ እያደረሱት ያለው ጉዳት እጅግ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡

በተለይም በእግረኛ መንገድና በተሸከርካሪ መተላለፊያ መስመሮች ላይ የግንባታ ግብዓቶችና ተረፈ-ምርቶችን የሚያከማቹ የሥራ ተቋራጮችና በለንብረቶች የእግረኞችን በመንገድ ሃብት በአግባቡ የመጠቀም መብትን ከመጋፋትና በከፍተኛ ወጪ የተገነባውን የከተማዋን ህዝብ የጋራ መጠቀሚያ የመንገድ ሃብት ከመጉዳት ባሻገር የትራፊክ አደጋ እንዲከሰት ምክንያት እየሆነ ይገኛል፡፡

ከዚህም በተጨማሪ የኮንክሪት ሚክሰር የሚያጓጉዙ ተሸከርካሪዎችን ጨምሮ የተለያዩ የግንባታ ግብዓቶችና ተረፈ-ምርቶችን ከቦታ ወደ ቦታ የሚያጓጉዙ የጭነት ተሸከርካሪዎች አፈር፣ ጠጠርና አሸዋ የመሳሰሉ ጭነቶችን በየጎዳናው ላይ እየበተኑ የሚያጓጉዙ በመሆኑና ከግንባታ ሳይቶች በተሸከርካሪዎች ጎማ አማካኝነት ይዘውት የሚወጡትን ጭቃና አፈር ጭምር በከተማዋ መንገዶች ላይ እያራገፉ የሚጓዙ በመሆኑ የከተማዋን የመንገድ ሃብት በእጅጉ እየተጎዳ ይገኛል፡፡

ስለሆነም በከተማዋ በተለያዩ የግንባታ ሥራዎች ላይ እየተሳተፉ የሚገኙ አካላት ድርጊቱ በከተማዋ የመንገድ ሃብት፣ ፅዳት መጓደል እና ከሁሉም በላይ ደግሞ በነዋሪዎች እንቅስቃሴ ላይ እያሳደረው የሚገኘውን ተፅእኖ በመገንዘብ አፋጣኝ የማስተካከያ እርምጃ እንዲወስዱ ባለሥልጣን መስሪያቤቱ በጥብቅ ያሳስባል፡፡

ከግንባታ ሥራዎች እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ በመንገድ ሃብት ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት፣ በመንገድ ዳር የውሃ መፋሰሻ መስመሮች ላይም የመደፈን አደጋ እየገራረጠ በመሆኑ በመጪው የክረምት ወራት ለጎርፍ አደጋ ስጋት ምክንያት እንዳይሆን ከወዲሁ መልክ ማስያዝ ይገባል፡፡

በመሆኑም በከተማዋ ደንብና ሥርዓት የማስከበር ኃላፊነት የተሰጣቸው አካላትና የሚመለከታቸው የከተማ አስተዳደሩ አስፈፃሚ ተቋማት ተገቢውን ቁጥጥርና ክትትል በማድረግ ህገ-ወጥ ድርጊቱን በመከላከል የበኩላቸውን እገዛ እንዲያደርጉ ባለሥልጣኑ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.