ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ባለፉት አስር ወራት ከ690 ኪሎ ሜትር በላይ የመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎች አከናውኗል
አዲስ አበባ፣ ግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ.ም፣- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አመራሮች የ10 ወራት የመንገድ መሰረተ ልማት የእቅድ አፈፃፀም ላይ ውይይት አካሄዱ፡፡
የባለስልጣኑን የአስር ወራት የእቅድ አፈፃፀም ያቀረቡት የእቅድ በጀትና እስትራቴጂክ ማኔጅመንት ዳይሬክተር አቶ መስፍን ከበረ እንደገለፁት ባለስልጣኑ ባለፉት አስር ወራት ውስጥ 694.3 ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ልዩ ልዩ የግንባታና የጥገና ስራዎችን ለመስራት አቅዶ 690.3 ኪ.ሜ በማከናወን የእቅዱን 99 በመቶ ለማሳካት መቻሉን ገልፀዋል፡፡
ዳይሬክተሩ አያይዘውም የመንገድ ግንባታና ጥገና ስራዎች የተሻለ አፈፃፀም እንደነበራቸው ገልፀው በቀጣይም ቀሪ ስራዎችን በተያዘላቸው ጊዜ ለማጠናቀቅ ሁሉም የስራ ክፍሎች በትጋት መስራት እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል፡፡
በውይይቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ በበኩላቸው ባለፉት አስር ወራት በተሻለ አፈፃፀም የተመዘገቡ ስራዎችን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚያስፈልግ ገልፀው ቀሪ ስራዎችን በአጭር ጊዜ በማጠናቀቅ የተቋሙን ውጤታማነት አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም በቀጣይ ክረምት ወራት የሚከሰት የጎርፍ ስጋት ለመከላከል ባለስልጣኑ እየሰራቸው ያሉ ስራዎች አጠናክሮ በማስቀጠል በመዲናዋ ነዋሪዎች ሕይወትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳይደርስ በልዩ ትኩረት መስራት ይጠበቅብናል ብለዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity