+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ቦሌ ሆምስ-ጎሮ ሌላው የመዲናዋ የመንገድ መረብ ማስተሳሰሪያ ፕሮጄክት

የአዲስ አበባ ከተማን የመንገድ መረብ ይበልጥ በማስተሳሰር ቀልጣፋና ምቹ የትራፊክ ፍሰት እንዲኖር እና የከተማዋን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እድገት በማፋጠን ዘመናዊ የከተማ ገፅታ ለመፍጠር እየተገነቡ ከሚገኙ በርካታ የመንገድ ፕሮጄክቶች መካከል የቦሌ ሆምስ-ጎሮ የመንገድ ግንባታ ፕሮጄክት ይገኝበታል፡፡

ይህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጄክት ከቦሌ ብራስ የቀለበት መንገድ መጋጠሚያ ተነስቶ በቦሌ ኤርፖርት በኩል ወደ ጎሮ ውጨኛው ቀለበት መንገድ የሚደርስ በአጠቃላይ 4.9 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው አዲስ የመንገድ መስመር ነው፡፡

ፕሮጄክቱ በዋናነት በከተማዋ በምስራቅ አቅጣጫ የውጨኛውን የቀለበት መንገድ ክፍል ከውስጠኛው የቀለበት መንገድ ጋር የሚያስተሳስር አቋራጭ አዲስ የመንገድ መረብ አካል በመሆኑ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳው ከፍ ያለ ነው፡፡

በተለይም ከቱሉ ድምቱ የክፍያ መንገድ አቅጣጫ ወደ አዲስ አበባ የሚገቡና የሚወጡ ተሽከርካሪዎች የትራፊክ መጨናነቅና እንግልት ሳይገጥማቸው ምቹ እና አቋራጭ በሆነ መንገድ በቀጥታ ወደ መሀል ከተማ ለመግባትና ለመወጣት የሚስችል አማራጭ መንገድ በመሆኑ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ፋይዳው የጎላ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

የቦሌ ሆምስ-ጎሮ የመንገድ ግንባታ ፕሮጄክት ከቦሌ ኤር ፖርት ከፍ ብሎ በስተግራ በኩል ከገርጂ ሮባ ዳቦ የመንገድ መረብ ጋር እንዲተሳሰር ተደርጎ እየተገነባ የሚገኝ በመሆኑ በአካባቢው ያለውን የትራፊክ ፍሰት በማቀላጠፍ በኩል ከፍተኛ ድርሻ እንደሚኖረው ይታመናል፡፡

ይህ የመንገድ ግንባታ ፕሮጄክት 60 ሜትር የጎን ስፋት ያለው ሲሆን፣ ምቹ የእግረኛ መንገድ እና የእፅዋት ስፍራ እንዲሁም የሞተር አልባ ትራንስፖርት እንቅስቃሴን ለማበረታታት የሚያግዝ የፔዳል ሳይክል መተላለፊያ መንገድን አካቶ እየተገነባ የሚገኝ ነው፡፡

ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በተመደበ ከ1.6 ቢሊዮን ብር በላይ በጀት አሰር ኮንስትራክሽን በተባለ ሀገር በቀል የስራ ተቋራጭ እየተገነባ የሚገኘው ይህ ፕሮጄክት፣ ከቦሌ ብራስ የቀለበት መንገድ መጋጠሚያ ጀምሮ 1.3 ኪሎ ሜትር የሚሆነው የመንገዱ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ አስፋልት ለብሶ አገልግሎት እየሰጠ የሚገኝ ሲሆን በቀሪው የመንገዱ ክፍል ላይ ደግሞ የአፈር ቆረጣ፣ የድሬኔጅ መስመር ዝርጋታና የድጋፍ ግንብ ስራዎች በመከናወን ላይ ናቸው፡፡

የፕሮጀክቱን የማማከርና የክትትል ስራውን ዩኒኮን አማካሪ ድርጅት እያከናወነው ሲሆን አሁን ላይ የፕሮጄክቱ አፈፃፀም 39.2 በመቶ ላይ ደርሷል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.