+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ባለግርማ ሞገሱ የአቃቂ ወንዝ ተሻጋሪ ድልድይ

የቡልቡላ የጋራ መኖሪያ ቤቶችን ከቂሊንጦ እስከ ቱሉ ድምቱ ያለውን አካባቢ ማስተሳሰሪያ ገመድ የሚሆነው ግዙፉና ባለ ግርማ ሞገሱ የአቃቂ ወንዝ ተሻጋሪ ድልድይ ግንባታ ተጠናቆ አገልግሎት ለመስጠት ከጫፍ ደርሷል፡፡

ተሻጋሪ ድልድዩ 325 ሜትር ርዝመትና 34 ሜትር የሚጠጋ የጎን ስፋት ያለው ሲሆን ከመሬት ወለል በላይ እስከ 43 ሜትር የሚደርስ ከፍታም አለው፡፡

ይህ ተሻጋሪ ድልድይ የቃሊቲ አደባባይ -ቡልቡላ ቂሊንጦ አደባባይ የመንገድ ፕሮጀክት አንዱ አካል ሲሆን የድልድዩ የግራ ክፍል ላይ ፕሪካስት የማስቀመጥ ስራ እየተከናወነ ይገኛል፡፡ የብረትና የአርማታ ስራዎችንም በቀጣይ አጭር ጊዜ ውስጥ ለማጠናቀቅ እየተሰራ ይገኛል፡፡ በተመሳሳይም የተሻጋሪ ድልድዩ የቀኝ መስመር የገርደር ስራዎች ተጠናቀው ፕሪካስት ለማስቀመጥ ዝግጅት ተጠናቋል፡፡

በዚሁ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ላይ እየተገነባ የሚገኘው ሌላው የቡልቡላ ወንዝ ድልድይም በጥሩ የአፈፃፀም ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ድልድዩ 175 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን የድልድዩ የግራ መስመር ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መጠናቀቅ ችሏል፡፡ በቀኝ በኩል ያለው የድልድዩ ክፍልም ድልድዩን የሚሸከሙት ማማዎች ግንባታ በመጠናቀቁ ገርደር የማስቀመጥ ስራ በቀጣይ አጭር ጊዜ የሚጀመር ይሆናል፡፡

የቃሊቲ አደባባይ -ቡልቡላ ቂሊንጦ አደባባይ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በአጠቃላይ 10.5 ኪ.ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን ከ40 እስከ 50 ሜትር የሚደርስ የጎን ስፋትም አለው፡፡

የግንባታ ስራውን የቻይናው ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ ሲያከናውነው የማማከርና የቁጥጥር ስራውን ደግሞ ሀይዌይ ኢንጂነርስ አማካሪ ድርጅት እየተከታተለው ይገኛል፡፡ አሁን ላይ የመንገድ ፕሮጀክቱ አጠቃላይ የግንባታ አፈፃፀም 84 በመቶ ላይ ድርሷል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ ግንባታ ሙሉ በሙሉ ሲጠናቀቅ በኮዬ ፈቼና በቂሊንጦ አከባቢ የሚገኙ ነዋሪዎችን ከቡልቡላ የጋራ መኖሪያ ቤቶች እና አካባቢው ጋር በቀጥታ በማስተሳሰር ወደ መሀል ከተማ የሚደረገውን እንቅስቃሴ የሚያሳልጥ በመሆኑ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጠቀሜታ ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.