+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

ቋሚ ኮሚቴው በመንገድ መሰረተ ልማት ዘርፍ የሚያጋጥሙ ችግሮች እንዲፈቱ በክትትና ድጋፍ ስራዎች አስፈላጊውን ድጋፍ ያደርጋል

የተከበሩ ወ/ሮ ልዕልቲ ግደይ

አዲስ አበባ፤ ሚያዝያ 5 ቀን 2015 ፣- በመንገድ መሰረተ ልማት ግንባታ ዘርፍ የሚያጋጥሙ ችግሮችን ለመፍታት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት የመሰረተ ልማትና የትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የሚያደርገውን ክትትልና ድጋፍ ስራ ወደፊትም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ወ/ሮ ልዕልቲ ግደይ ገለፁ፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባላት በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ የሚገኙ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን የዘጠኝ ወራት አፈፃፀም እና ለጎርፍ አደጋ ስጋት ተጋላጭ ይሆናሉ ተብለው በተለዩ ቦታዎች እየተሰሩ የሚገኙ የቅድመ-መከላከል ሥራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

ጉብኝቱን የመሩት የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወ/ሮ ልዕልቲ ግደይ በከተማዋ በግንባታ ላይ የሚገኙት የመንገድ ፕሮጀክቶች የተሻለ አፈፃፀም ላይ መድረሳቸውን ጠቁመው፣ ቋሚ ኮሚቴው በግንባታ ስራ ወቅት እያጋጠሙ የሚገኙ ችግሮች በወቅቱ እንዲፈቱ የክትትልና ድጋፍ ስራዎችን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

ለምክር ቤቱ አባላት ገለፃ ያደረጉት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጅነር ሞገስ ጥበቡ በበኩላቸው ባለፉት 9 ወራት ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በአጠቃላይ 606 ኪሎ ሜትር የግንባታ እና ጥገና ስራዎች መከናወኑን ገልፀዋል፡፡

አሁን ላይ እየተራዘመ የመጣው የበልግ ወቅት ዝናብ በመንገድ ግንባታና ጥገና ሥራዎች አፈፃፀም ላይ ተፅዕኖ እያሳደረ ቢሆንም ተቋሙ በዕቅድ የያዛቸውን ተግባራት ለማሳካት በቀሪዎቹ የበጋው ጊዜያት የጀመረውን ጥረት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

ዋና ዳይሬክተሩ አክለውም የመሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በየጊዜው በሚያካሂደው የክትትልና ድጋፍ ሥራ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶች የመገጥሟቸው ችግሮች እንዲፈቱ በማድረግ በኩል እያደረገ ላለው ድጋፍ ምስጋናቸውን በማቅረብ በቀጣይም የሚደረገው ድጋፍ እና ክትትል ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል፡፡

የቋሚ ኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ ሳምሶን ወንድምነህ ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ በከተማው እየሰራቸው የሚገኙት የመንገድ ፕሮጀክቶች በጥሩ አፈፃፀም ላይ መድረሳቸውን ገልፀው፣ ለጎርፍ ተጋላጭ የሆኑ የከተማዋ የተለያዩ አከባቢዎች ላይ የሚከናወኑ የግንባታና ጥገና ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.