+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

የቃሊቲ አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ግንባታ እየተፋጠነ ነው

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም፡- የደቡብ አዲስ አበባ ክፍል ዋነኛ የወጪ ገቢ ኮሪዶር ሆኖ ለረጂም ዓመታት ሲያገለግል የቆየው ነባር መንገድ ማሻሻያ አካል የሆነው የቃሊቲ አደባባይ – ቱሉ ዲምቱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ግንባታ በመፋጠን ላይ ነው፡፡

በመንገድ ፕሮጀክቱ የግራ መስመር በተለያዩ የመንገድ ግንባታው ሴክሽኖች ላይ 5 ኪሎ ሜትር የሚሆነው የመንገዱ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ የአስፋልት ንጣፍ የለበሰ ሲሆን፣ በቀሪው 6 ኪሎ ሜትር የመንገዱ ክፍል ደግሞ የሰብ ቤዝ፣ የቤዝ ኮርስ እና የከርቭ ስቶን ስራዎች ተገባደው አስፋልት ለማንጠፍ ዝግጅት እየተደረገ ይገኛል፡፡

ባለስልጣን መስሪያቤቱ የዚህን የመንገድ ፕሮጀክት ቀሪ የግንባታ ስራዎች በአጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ በትኩረት እየሰራ ሲሆን፣ አሁን ላይ የፕሮጀክቱ አጠቃላይ የፊዚካል አፈፃፀም 62 በመቶ ደርሷል፡፡

ይህን የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ቻይና ኮሙኒኬሽን ኮንስትራክሽን ካምፓኒ የተባለ ሥራ ተቋራጭ እየተገነባ ሲሆን፣ የፕሮጀክቱን ማማከርና ቁጥጥር ስራ ደግሞ ኢንጂነር ዘውዴ አማካሪ ድርጅት እየተከታተለው ይገኛል፡፡

ፕሮጄክቱ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዳይጠናቀቅ እንቅፋት የሆኑት ከፋይናንስ እና ከወሰን ማስከበር ጋር የተያያዙ ችግሮች በመፈታታቸው አሁን ላይ ግንባታው በከፍተኛ ፍጥነት በመከናወን ላይ ነው፡፡

የቃሊቲ -ቱሉዲምቱ የመንገድ ግንባታ ፕሮጄክት በአጠቃላይ 10.9 ኪ.ሜ ርዝመትና 50 ሜትር የሚደርስ የጎን ስፋት ያለው ሲሆን፣ ቀደም ሲል ከቃሊቲ አደባባይ ወደ ቱሉ ዲምቱ አደባባይ በስተቀኝ ያለው የመንገዱ ክፍል የመጀመሪያ ደረጃ የአስፋልት ንጣፍ ስራ ተከናውኖለት የትራፊክ አገልግሎት እንዲሰጥ መደረጉ ይታወሳል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity

ኢንስታግራም፡- https://www.instagram.com/addisababaroads/

Comments are closed.