ጀርመን አደባባይ አካባቢ በሚገኘው ወንዝ ዳርቻ በሚከናወን ህገወጥ ተግባር ምክንያት በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ የጎርፍ አደጋ ስጋት ደቅኗል
አዲስ አበባ፣ ሚያዝያ 28 ቀን 2015 ዓ.ም ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በድልድዮች እና በወንዞች ዳርቻ አካባቢ በሚደፋ የግንባታ ተረፈ ምርት፣ አፈርና ደረቅ ቆሻሻ ምክንያት ጎርፍ አደጋ ስጋት ያለባቸውን አካባቢዎች በመለየት የጥገና እና የማስተካከያ ስራዎች እያከናወነ የሚገኝ ቢሆንም የችግሩ አሳሳቢነት ግን አሁንም እንደቀጠለ ነው፡፡
በተለምዶ ጀርመን አደባባይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ በሚገኘው ድልድይ ስር በተደጋጋሚ ጊዜያት በሚደፋው አፈር፣ ቆሻሻና የግንባታ ተረፈ ምርት ሳቢያ የወንዙ ተፈጥሯዊ የመፋሰሻ መስመር እየጠበበ በመምጣቱ አሁን ላይ የጎርፍ አደጋ ስጋቱን አሳሳቢ አድርጎታል።
የወንዙን ዳርቻ ተከትሎ በአካባቢው ለሚከናወነው የእርሻ ሥራ እንቅስቃሴ አገልግሎት የሚደፋው ተጨማሪ አፈር የጎርፍ አደጋ ስጋቱ እንዲባባስ ምክንያት ሆኗል።
ከአንድ ዓመት በፊት በአካባቢው በተከሰተ የጎርፍ አደጋ የሰዎች ህይወት ማለፉና በንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱ የሚታወስ ነው፡፡
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ተመሳሳይ የጎርፍ አደጋ እንዳይፈጠር በድልድዩ ስር ለረጅም ጊዜ የተከማቸውን እና ከፍተኛ መጠን ያለውን ቆሻሻ እና ደለል አፈር በማንሳት ወንዙ ተፈጥሯዊ ፍሰቱን ጠብቆ እንዲጓዝ የሚያስችል የቅድመ አደጋ መከላከል ሥራ መስራቱ ይታወሳል፡፡
ይሁን እንጂ በወንዙ ዳርቻ የሚከናወነው ህገወጥ እንቅስቃሴ ተባብሶ በመቀጠሉ በወንዙ ዳርቻ በሚኖሩ ነዋሪዎች ላይ ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ እንዳይከሰት ስጋት መፍጠሩን የደቡብ አዲስ አበባ መንገድ ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር ኢንጂነር ህይወት ሳሙኤል ገልፀዋል፡፡
በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር አካላት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በሰው ህይወትና ንብረት እንዲሁም በመንገድ ሀብቱ ላይ የጎርፍ አደጋው ሊያደርስ የሚችለውን አደጋ ከዐዲሁ ለማስቀረት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ኢንጂነር ህይወት አሳስበዋል፡፡
በተመሳሳይም በሌሎች የወንዞች መፋሰሻ መስመሮችና በድልድዮች አካባቢ የሚከናወኑ ህገ-ወጥ ተግባራት የጎርፍ አደጋ ስጋት በመደቀን በሰው ህይወት፣ በንብረትና በመንገድ መሰረተ-ልማት ላይ ጉዳት እንዳያስከትሉ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት እና የአካባቢው ነዋሪዎች የበኩላቸውን አዎንታዊ ሚና እንዲወጡ ባለስልጣኑ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity