በወንዞች ዳርቻ እና ድልድዮች ላይ በሚፈፀሙ ህገወጥ ተግባራት ድልድዮች ለጉዳት እየተጋለጡ ይገኛሉ
አዲስ አበባ፣ የካቲት 11 ቀን 2015 ዓ.ም፡- በአዲስ አበባ ከተማ የሚገኙ ድልድዮች ወደ ወንዝ በሚደፋ አፈር፣ቆሻሻ እና የግንባታ ተረፈ ምርት ምክንያት ለጉዳት እየተጋለጡ ይገኛሉ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ድልድዮችን ከመጠገን በተጨማሪ በድልድዮች ላይ የሚፈፀሙ ህገወጥ ተግባራትን የመከላከል ስራዎችን የሚያከናውን ቢሆንም የችግሩ አሳሳቢነት ግን እንደቀጠለ ነው፡፡
በተለምዶ ወርቁ ሰፈር ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ገላን ካባ መሸጋገሪያ ድልድይ ቡልቡላ ወንዝ ዳርቻ በሚደፋ አፈር፣ የግንባታ ተረፈ ምርት እና ቆሻሻ ወንዙ በደለል በመሞላቱ ድልድዩ የመፍረስ ስጋት ላይ እንዲሚገኝ የደቡብ አዲስ አበባ መንገድ ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር ኢንጂነር ህይወት ሳሙኤል ገልፀዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ በሚደፋ አፈር፣የግንባታ ተረፈ ምርት እና ቆሻሻ ወንዙን ሙሉ በሙሉ በመገደቡ የወንዙን ተፈጥሯዊ ፍሰት በማስተጓጎል፣ የወንዙ መፋሰሻ መስመር እንዲጠብና የውሃ ፍሰት አቅጣጫ እንዲቀየር በማድረግ በወንዙ ዳርቻ ለሚኖሩ ነዋሪዎች ድንገተኛ የጎርፍ አደጋ ያስከትላል ብለዋል፡
በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደርና የፀጥታ አካላት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በወንዙ ዳርቻ አፈር፣ ቆሻሻና የግንባታ ተረፈ ምርት በሚደፉ ግለሰቦች እና ተቋማት ላይ የእርምት እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ በመንገድ ሀብት፣ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የሚከሰተውን አደጋ ለማስቀረት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ማሳወቃቸውን ኢንጂነር ህይወት አያይዘውገልፀዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም:- https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ :- https://www.facebook.com/AbabaCity
ትዊተር :- https://twitter.com/AbabaCity