+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን አመሰራረት ታሪክ

የአዲስ አበባ ከተማ የመንገድ ግንባታ ታሪክ ከመዲናዋ ምስረታ ይጀምራል፡፡ ከተማችን በ1879ዓ.ም በዳግማዊ ምንሊክ  ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮዽያ ዘመነ መንግስት፤ በእቴጌ ጣይቱ ሀሣብ አመንጭነት እንደተመሠረተች ታሪክ ይነግረናል፡፡

ለከተማዋ መመሥረት መነሻዋ የፊንፊኔ ፍል ውሃ ናት፡፡ እቴጌዩቱ ከእንጦጦ ቤተመንግስታቸ ው ደቡባዊ አቅጣጫ ሲያማትሩ ጥጥ የመሰለ ብናኝ ሲንቦለቦል በማየታቸው ከተራራው ወረዱ፡፡ ከፊንፊኔ ፍል ውሃ ፊንፊን የሚለው የውሃ ሙቀት ነፍሳቸውን ማረከውና ከንጉሰ ነገስቱ አስፈቅደው ቤት መገንባት ጀመሩ፡፡ ንጉሱን ተከትለው በዙሪያ ከሰፈሩ መኳንንት፤ የጦር አበጋዞችና ሠራዊቶቻቸው፤ ልዩ ልዩ ባለሙያዎችና የውጭ ሀገር መልዕክተኞች መኖሪያዎች በመመስረታቸው፤ ከአንዱ ቤት ወደ ሌላው፤ ከዚያኛው ሰፈር ወደ እዚህኛው ለሚከናወንና በእግረኛም ሆነ በእንሰሳት ለሚደረግ እንቅስቃሴ መንገድ በማስፈለጉ የመንገድ ግንባታውም በዚያው ልክ ትኩረት ስለማግኘቱ በስፋት ተዘግቧል፡፡

በተለይም በ1894 አካባቢ ከአዲስዓለም ቤተ መንግስት እስከ አዲስአበባዋ የምንሊክ ቤተመንግስት ድረስ ያለውን ርቀት ለማቀራረብ ዘመናዊ ሊባል የሚችለው የመጀመሪያው መንገድ ግንባታ ለዘርፉ ዕድገት ትኩረት ስለመስጠቱ ዋነኛ ማሣያ ነው፡፡

በመንገድ ግንባታው ላይ ራሳቸው ንጉሠ ነገስቱም ንጣፍ ተነጥፎ፤ ዙፋን ተዘርግቶ እና ድባብ ተይዞላቸው እግር ለእግር የመንገድ ግንባታውን የመቃኘት ሥራቸው አንዱ ሆኖ አስፈላጊ በሆነበት ቦታ ሁሉ ድንጋይ ተሸክመው ያግዙ እንደነበር ታላቁ ጋዜጠኛ ጳውሎስ ኞኞ “አጤምንሊክ” በተባለው ታሪካዊ መጽሀፍ ላይ አስቀምጦታል፡፡ ንጉሠ ነገስቱ የመንገድ ግንባታው በተሻለ ሁኔታ እንዲከናወንም በ1896ዓ.ም ከፍተኛ ቁጥር ባላቸው ሠራተኞች የሚንቀሣቀስ የድንጋይ መዳመጫ /ሮለር/ ከውጭ ገዝተው በማስመጣት በዙሪያቸው ባሉ የውጭ ሀገር ኤምባሲዎችና የተለያዩ አቅጣጫዎች የተሻሉ ጥርጊያ የመንገድ ግንባታዎች ተከናውነዋል፡፡

ዳግማዊ አጼ ምንሊክ የመንገድ ግንባታውን በዚህ መልክ ጀምረው ከአውሮፓ በቁጥር 2 ተሽከርካሪዎችን ለመጀመሪያ ጊዜ በማስገባት በዚሁ መንገድ ላይ እንዲነዱ አድርገዋል፡፡

እንግዲህ በዚህ አግባብ የተጀመረው የመንገድ ግንባታ ዘመናዊ ቅርጽ የያዘው በቀዳሚዊ አጼ ኃይለስላሴ ዘመነ መንግስት ነው፡፡ ንጉስ ነገስቱ መንገድ የስልጣኔ መገለጫ መሆኑን በመገንዘባቸው እና የከተማዋ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ እንቅስቃሴ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መምጣት ሥራውን አቅጣጫ ለማስያዝና በተደራጀ አኳሀን ለመምራት እንዲቻል በተቋቋመው የማዘጋጃ ቤት ውስጥ “ህዝባዊ ሥራዎች ክፍል” /public works department/ በማደራጀት በከተማዋ የሚከናወነውን የመንገድ ግንባታ በአግባቡ ለመምራት አስችሏል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞ በ1934ዓ.ም በከተማዋ ከንቲባ የሚመራ የመንገድ ግንባታ ጥገናና አስተዳደር ሥራዎች ሙሉ በሙሉ በማዘጋጃ ቤቱ እንዲፈፀምና በሁዋላም “የመንገድና ህንጻ ግንባታ ሥራ መምሪያ” በማደራጀት እንዲከናወን ተደርጓል፡፡ በዚህ አደረጃጀት ምክንያት ከመስቀል አደባባይ ቦሌ፤ ከጦርሀይሎች መገናኛ፤ ከመስቀል አደባባይ ሽሮሜዳን የመሣሠሉ ሰፋፊ መንገዶች ተሠርተዋል፡፡

የ1966ቱን ህዝባዊ አብዮት ተከትሎ ወደ ሥልጣን የመጣው ወታደራዊ ደርግ የሶሺዮ ኢኮኖሚውና የፖለቲካ ቅኝቱ የምሥራቅ አውሮፓ ሶሻሊስት ርዕዮት በመሆኑ የሥራ ውጤቱም በአብዛኛው ይህንኑ መሠረት ያደረገ ነበር፡፡ አዳዲስ ግንባታዎችን ከማከናወን ይልቅ በአብዛኛው ነባር መንገዶችን የመጠገንና የማሻሻል ሥራዎችን አከናውኗል፡፡ በተለይ ከአዲስ አበባ ምስረታ 1ዐዐኛ ዓመት በዓል ጋር ተያይዞ በታሪካዊ አካባቢዎች ለምሣሌ እንጦጦ፣ አድዋ ድልድይ አካባቢ አዳዲስ መንገዶች ተሠርተዋል፡፡ ያም ሆኖ እስከ 1983ዓ.ም የሥርዓት ለውጥ ድረስ መዲናዋ ለ1ዐ4 ዓመታት የገነባችው መንገድ ከሚያስፈልጋት 5 በመቶውን ብቻ ነው፡፡

አዲስ አበባ ካላት አጠቃላይ 54ሺህ ሄክታር መሬት ስፋት አንጻር በዘመናዊ መለኪያ ቢያንስ 25 በመቶው ወይም ከ4-1 እጅ በመንገድ መሸፈን አለበት የሚል ዓለም ዐቀፍ ስምምነት አለ፡፡ ይሁን እንጂ በ1983ዓ.ም መዲናዋ ሊኖራት ከሚገባው ሽፋን 5 በመቶ ብቻ ቢሆንም በ1985ዓ.ም በአዋጅ ቁጥር 41/85 መሠረት የማዕከልና የክልል አስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር ሲወሰን አዲስ አበባም ራሷን በራሷ እንድታስተዳድር መብት አግኝታለች፡፡ ይህ አጋጣሚ መዲናዊ በመንገድ ዘርፍ የአቅምም የአስተሣሠብም ፓራዳይም ሺፍት ያገኘበት ጊዜ ነው ማለት ይቸላል፡፡ ለዚህ ዋነኛ አብነት የሚባለው የቀለበት መንገድ ግንባታ መጀመር ነው፡፡

መዲናችን አዲስ አበባ የቀለበት መንገድን ጨምሮ በርካታ የግንባታና የጥገና ሥራ በመጀመሯ ምክንያት የአደረጃጀት ለውጥ አድርጋለች፡፡ ይህን ዓለም አቀፍ ንጽጽር ያለውን የቀለበት መንገድና ሌሎች ኘሮጀክቶችን በአግባቡ ለመምራት በዋንኛነትም የዲዛይን፣ የግንባታ እና የአስተዳደር ሥራዎችን አደራጅቶ ለመሥራት እንዲቻል የከተማው አስተዳደር በደንብ ቁጥር 7/1990 ዓ.ም የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለልጣንን አቋቁሟል፡፡