15ኛው ብሄራዊ የሰንደቅ ዓላማ ቀን በባለስልጣን መስርያ ቤቱ ተከበረ
አዲስ አበባ፣ ጥቅምት 7 ቀን 2015ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን 15ኛውን የብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ቀን “ሰንደቅ ዓላማችን የብዙኃነታችን መገለጫ የሉዓላዊነታችን ምሰሶ ነው” በሚል መሪ ቃል በዛሬው ዕለት በድምቀት ተከብሯል፡፡
የባለስልጣን መስርያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ በስነስራዓቱ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልዕክት፤ የዘንድሮው የሰንደቅ ዓላማ ቀን የውስጥ አፍራሽ ኃይሎችን የተላላኪነት እኩይ ድርጊት እና የውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ያለማቋረጥ፣ በቅንጅት እያስፈፀሙ ያሉትን ሀገር የማፍረስ እኩይ ሴራ እየታገልን፤ በአንፃሩ አይቻሉም የሚባሉ ታላላቅ የልማት ስኬቶችን በማስመዝገብ ወደ ብልፅግና የምናደርገውን ግስጋሴ እያስቀጠልን በምንገኝበት ወቅት ላይ የሚከበር በመሆኑ ልዩ ትርጉም እንደሚሰጠው ገልፀዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ አያይዘውም የባለሥልጣን መስሪያቤቱ ሰራተኞች ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማችንን ከማክበርና ከማስከበር ጎን ለጎን በተሰለፍንበት የሥራ መስክ ጠንክረን በመስራት፣ ከመንግስትና ከህዝብ የሚጠበቅብንን የመንገድ መሰረተ-ልማት ማስፋፋት ተልዕኮ በላቀ ደረጃ ለመወጣት ሌት ተቀን የምንተጋ መሆኑን በዚህ አጋጣሚ በድጋሚ እናረጋግጣለን ብለዋል፡፡
የሥነስርዓቱ ተሣታፊዎች በበኩላቸው፤ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ በማድረግ በየጦር ግንባሩ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያዊነት እየተዋደቀ ለሚገኘው ለጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊታችን እና ለጥምር ጦሩ ያላቸውን ከፍ ያለ አክብሮት በመግለፅ በትግሉ ሂደት ለተሰው የሰራዊቱ አባላት የአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት አድርገዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም: https://t.me/AddisRoads
ፌስ ቡክ : https://www.facebook.com/AbabaCity