+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

የግንባታ ፍጥነትን ከጥራት ጋር አዋህዶ የተጠናቀቀው የፑሽኪን አደባባይ -ጎተራ ማሳለጫ የመንገድ ፕሮጀክት

አዲስ አበባ፡- ነሀሴ 9 ቀን 2014 ዓ.ም፡- የአሌክሳንደር ፑሽኪን አደባባይ ጎተራ ማሳለጫ መንገድ የፕሮጀክት አፈፃፀም ፍጥነትን ከጥራት ጋር በማዋሀድ የግንባታ ሂደቱ ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ በዛሬው ዕለት የፌዴራልና የከተማዋ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎችን ጨምሮ ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት በይፋ ተመርቋል፡፡

በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አበቤ በከተማችን የመንገድ ግንባታ ታሪክ ውስጥ በዓይነቱ ልዩ የሆነው የፑሽኪን አደባባይ ጎፋ ማዞሪያ -ጎተራ ማሳለጫ የመንገድ ፕሮጀክትን ስናስመርቅ የሀገራችን የህዳሴ ግድብ የትውልድ አሻራ በዓለም አደባባይ ደምቆ በታየበት ማግስት በመሆኑ ልዩና ታሪካዊ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

የፑሽኪን አደባባይ-ጎፋ ማዞሪያ-ጎተራ ማሳለጫ የመንገድ ፕሮጀክት እስካሁን ድረስ በከተማዋ ከተገነቡት መንገዶች በግንባታ ጥራቱም ሆነ በፕሮጀክት አፈፃፀም ፍጥነቱ ተወዳዳሪ የሌለው ከመሆኑም በላይ የከተማዋን አንፀባራቂ ለውጥ አመላካች መሆኑን ክብርት ከንቲባዋ አክለው ገልፀዋል፡፡

ክብርት ከንቲባዋ በመንገድ ፕሮጀክቱ ላይ ከሌሎች የፌደራልና የከተማዋ ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች ጋር በመሆን ችግኝ በመትከል የአረንጓዴ አሻራቸውንም አስቀምጠዋል፡፡ በተጨማሪም ወ/ሮ አዳነች አበቤ ለመንገድ ፕሮጀክቱ መሳካት ከፍተኛ ሚና ለነበራቸው አካላትም የእውቅና እና የምስጋና ሰርተፊኬት አበርክተዋል፡፡

በከተማ አስተዳደሩ የመንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሞገስ ጥበቡ በበኩላቸው የመንገድ ፕሮጀክቱን በተያዘለት ጊዜ ለማጠናቀቅ ከቀኑ የስራ ሰዓት በተጨማሪ ሌሊት ጭምርም በመስራት ከፍተኛ ርብርብ ተደርጎበታል ብለዋል፡፡

ቀደም ሲል ከፑሽኪን አደባባይ-ጎተራ ማሳለጫ ከፍተኛ የትራፊክ መጨናነቅ ችግር የነበረበት መሆኑን ያስታወሱት ኢንጂነር ሞገስ አሁን ላይ 320 ሜትር የመሬት ውስጥ መተላለፊያ ዋሻን አካቶ መሰራቱ የትራፊክ ችግሩን ከማቃለሉም በላይ የአካባቢውን ገፅታ የቀየረ ነው ብለዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የፈጣን አውቶቢስ መስመሮችን ጨምሮ የተገነባ በመሆኑም በቀጣይ የፍጥነት መንገዶቹ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ሲሆኑ ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ዋና ዳይሬክተሩ ጨምረው ገልፀዋል፡፡

ይህ የመንገድ ፕሮጀክት 3.8 ኪ.ሜ ርዝመትና ከ30-45 ሜትር የሚሆን የጎን ስፋት ያለው ሲሆን የግንባታ ስራውን ቻይና ፈርስት ሀይ ዌይ ኢንጂነሪንግ ከቻይና መንግስት በተገኘ ድጋፍ ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በተያዘለት የጊዜ ገደብ የጥራት ደረጃውን ጠብቆ አከናውኖታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ቴሌግራም: https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ : https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር : https://twitter.com/AbabaCity

Comments are closed.