+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

አሌክሳንደር ፑሽኪን አደባባይ -ጎተራ ማሳለጫ የመንገድ ፕሮጀክት ተመረቀ

አዲስ አበባ፡- ነሀሴ 9 ቀን 2014 ዓ.ም፡- ከ1.5 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተደረገበት የፑሽኪን አደባባይ-ጎፋ ማዞሪያ-ጎተራ ማሳለጫ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት በዛሬው ዕለት በይፋ ተመርቆ ለትራፊክ ክፍት ሆኗል፡፡

ይህ የመንገድ ፕሮጀክት 3.8 ኪ.ሜ ርዝመትና ከ30-45 ሜትር የሚሆን የጎን ስፋት ያለው ሲሆን የግንባታ ስራውን ቻይና ፈርስት ሀይ ዌይ ኢንጂነሪንግ በተያዘለት የጊዜ ገደብ የጥራት ደረጃውን ጠብቆ አከናውኖታል፡፡፡

ይህ ዘመናዊ የመንገድ ፕሮጀክት በከተማዋ የመንገድ ታሪክ ውስጥ የመጀመሪያው ሊያስብልለት የሚያስችል 320 ሜትር ርዝመት ያለው ዋሻ(Tunnel) እና ተጨማሪ የፈጣን አውቶቢስ መተላለፊያ መስመር (Bus Rapid Transit)፣ ከስርና ከላይ መተላለፍ የሚያስችሉ ሁለት ትላልቅ ማሳለጫ ድልድዮችም አሉት፡፡

ይህ የመንገድ ፕሮጀክት በአካባቢው የነበረውን የትራፊክ መጨናነቅ ችግር ከማቃለሉም ባሻገር የከተማዋን ገፅታ በመቀየር ረገድ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ተብሎ ይታመናል፡፡

የመንገድ ፕሮጀክቱ የግንባታ ስራ መስከረም 20 ቀን 2012 ዓ.ም መጀመሩ ይታወሳል፡፡

ፕሮጀክቱ በዛሬው ዕለት የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስትር አቶ አህመዲን ሽዴ፣ የትራንስፖርትና ሎጀስቲክ ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ ፣ ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች እና በኢትዮጲያ የቻይና አምባሳደር ቻርጅ ዲአፌርስ የሆኑት ሚስተር ሺን ኪንግማን በተገኙበት በታላቅ ድምቀት ተመርቋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ

ቴሌግራም: https://t.me/AddisRoads

ፌስ ቡክ : https://www.facebook.com/AbabaCity

ትዊተር : https://twitter.com/AbabaCity

Comments are closed.