በወንዞች ዳርቻ እና ድልድዮች አካባቢ የሚደፋ አፈር፣ ቆሻሻና የግንባታ ተረፈ ምርት ለጐርፍ አደጋ መከሰት ዋነኛ መንስኤ ሆኗል
ሚያዝያ 17 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ፡- በወንዝ ዳርቻዎች አካባቢ ባሉ ድልድዮች ዙሪያ በመፈፀም ላይ ያለው የአፈር መድፋት፣ ቆሻሻ መጣልና የግንባታ ተረፈ ምርት የማስወገድ ህገወጥ ተግባርመንገድ ላይ ለሚደርሱ የጎርፍ አደጋዎች መከሰት ዋነኛ መንስኤ እየሆነ ይገኛል፡፡በወንዝ ዳረቻዎችና ድልድዮች ስር የሚደፋ አፈር የወንዙን ተፈጥሯዊ ፍሰት በማስተጓጎል፣ የወንዞች መፋሰሻ መስመር እንዲጠብና የውሃ ፍሰት አቅጣጫ እንዲቀየር በማድረግ አደጋ ያስከትላል፡፡ በተለይ በዝናብ ወቅት በከተማዋ መንገዶች ላይ የጎርፍ አደጋ እንዲከሰት በማድረግ ከፍተኛ መዋዕለ ነዋይ ፈሶባቸው የተገነቡ የመንገድ መሰረተ-ልማቶች በቀላሉሉ ለብልሽት እንዲጋለጡ ከማድረጉም በተጨማሪ የትራፊክ እንቅስቃሴውን በማስተጓጎል የከተማችንን ነዋሪዎችን ላልተገባ እንግልት እየዳረገ ይገኛል፡፡ በዚህ ምክንያት በተደጋጋሚ የጎርፍ አደጋ እየተከሰተባቸው ከሚገኙ አካባቢዎች መካከል በቦሌ ክፍለ ከተማ በተለምዶ ጐላጐል ሪል ስቴት ወይም 72 መታጠፊያ በመባል በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው ድልድይ አንዱ ነው፡፡ ለጎርፍ ችግሩ መከሰት ዋነኛ ምክንያት የሆነው በአካባቢው የተደፋው ከፍተኛ መጠን ያለው አፈር፣ ቆሻሻና የግንባታ ተረፈ ምርት ሲሆን፣ ይህም በአካባቢው ከፍተኛ መጠን ያለው ቁልል ደለል በመፈጠሩ እና ድልድዩን በመዝጋቱ በዝናብ ወቅት ጐርፍ የወንዙን አቅጣጫ በመተው በድልድዩ ላይ በማለፍ ወደ መንገድ በመፍሰሱ ነው፡፡ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት በድልድዩ ስር የተከማቸውን ደለል አፈርና ቆሻሻ የማፅዳት ስራ ቢያከናውንም ህገ-ወጥ ተግባሩ ባለመቆሙ ችግሩ እየተባባሰ መጥቷል፡፡ በተመሳሳይም ባለፈው ዓመት በተከሰተ የጎርፍ አደጋ ለዜጎች ሞትና ንብረት መውደም ምክንያት በሆነው እና በተለምዶ ጀርመን አደባባይ ድልድይ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አሁንም በወንዙ ዳርቻ ላይ አፈር፣ ቆሻሻ እና የግንባታ ተረፈ-ምርት እየተደፋ በመሆኑ በመንገድ ሃብትና ንብረት ላይ ጉዳት እንዳያስከትል ከወዲሁ መፍትሄ ሊበጅለት ይገባል፡፡መጪው ጊዜ የበልግ ዝናብ ወቅትና ክረምት ወራት በመሆኑ በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደርና የፀጥታ አካላት ለጉዳዩ ተገቢውን ትኩረት በመስጠት በወንዞች ዳርቻ አካባቢ በሚከናወነው አፈርና፣ ቆሻሻና የግንባታ ተረፈ-ምርት የመድፋት ህገወጥ ተግባርን በመቆጣጠር በአጥፊዎች ላይ አስተማሪ ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ በማድረግ በመንገድ ሀብት፣ በሰው ህይወትና ንብረት ላይ የሚከሰተውን አደጋ ለማስቀረት የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ባለስልጣኑ መልዕክቱን ያስተላልፋል፡፡የከተማችን ነዋሪዎችም የጋራ መጠቀሚያችን ለሆነው የመንገድ ሃብት ደህንነት ሲባል ህገውጥ ድርጊት የሚፈፅሙ አካላትን በየአካባቢው ለሚገኙ የአስተዳደርና የፀጥታ አካላት እንዲሁም ለአዲስ አበባ መንገዶች ባለሥልጣን በነፃ የስልክ መስመር 8267 በመጠቆም የበኩላቸውን የዜግነት ድርሻ እንዲወጡ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ያሳስባል፡፡የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ማህበራዊ ትስስር ገፆችን ይቀላቀሉ
ቴሌግራም: https://t.me/AddisRoads