+251 11371 2982 aacracom@gmail.com

”ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በተለያዩ ምክንያቶች ለተጓተቱ የመንገድ ፕሮጀክቶች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት እየሰራ ይገኛል፡፡”

ኢንጅነር ሙህዲን ረሻድ የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር

የባለሥልጣኑ ስትራቴጂክ አመራር፣ በየደረጃው ያሉ የስራ መሪዎች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በግንባታ ላይ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

አዲስ አበባ፣ ህዳር 6 ቀን 2018 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለሥልጣን ስትራቴጂክ አመራርና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች በስራ ተቋራጮች እና በራስ ኃይል እየተገነቡ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን የግንባታ ሂደት ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

ጉብኝቱን የመሩት የባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሙህዲን ረሻድ፤ የጉብኝቱ ዋና ዓለማ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ በከተማዋን የተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶች የደረሱበትን ወቅታዊ የአፈፃፀም ደረጃ ለመቃኘትና እያጋጠሙ ለሚገኙ ችግሮች መፍትሄ በመስጠት የፕሮጀክቶቹን አፈጻጸም ለማፋጠን ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።

ኢንጂነር ሙህዲን አያይዘውም፤ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እየተገነቡ ያሉና በወሰን ማስከበርና በሌሎች ተያያዥ ችግሮች ምክንያት የተጓተቱ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት በመፍታት ለየህብረተሰቡ ጥያቄ አፋጣኝ ምላሻ ለመስጠት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡

ኢንጂነር ሙህዲን አክለውም፤ በስራ ተቋራጮች እየተገነቡ የሚገኙት የአየር ጤና -ወለቴ፣ የአይ.ሲ.ቲ ፓርክ – ቦሌ አራብሳ እና ሌሎች የመንገድ ፕሮጀክቶች በተለያዩ ምክንያቶች በታሰበው ፍጥነት እየተገነቡ አለመሆናቸውን አንስተው፤ በቀጣይ የስራ ተቋራጮቹ የተሻለ አፈፃፀም ማስመዝገብ ካልቻሉ ውል በማቋረጥ በራስ አቅም ገንብቶ ለትራፊክ ክፍት ለማድረግ ባለሥልጣን መስሪያ ቤቱ እንደሚሰራ በአፅዕኖት ተናግረዋል፡፡

በባለሥልጣኑ አመራሮች የመስክ ጉብኝት ከተደረገላቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል አየር ጤና- ወለቴ፣ አይሲቲ ፓርክ- አራብሳ፣ ፋኑኤል፣ በረከት፣ ወታደር ሰፈር፣ አራብሳ 5 እና 6፣ የካ ጣፎ፣ አያት ጨፌ የጋራ መኖሪያ ቤቶች የመንገድ ፕሮጀክቶች እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

Comments are closed.